ከ900 ሺህ በላይ ካታሎኒያውያን መገንጠልን ተቃውመው ሰልፍ ወጡ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ባለፈው ሳምንት በካታሎኒያ የተካሄደውን የካታሎኒያን ግዛት ከእስፓኝ የመገንጠል ሕዝበ ውሳኔን እና አጠቃላይ የመገንጠል ውሳኔን በመቃወም ከ900 ሺህ በላይ ሰልፈኞች ዛሬ በባርሴሎና እንደተሰለፉ ተገለጸ።

በሰሜናዊው ምስራቅ የእስፓኝ ግዛት የሆኑት ካታሎኒያውያን ባለፈው ሳምንት ከ43% በላይ ህዝብ በተሳተፈበት ህዝበ ውሳኔ ከ90% በላይ ከእስፓኝ መንግስት ተገንጥለው የራሳቸውን የካታሎኒያን ሪፐብሊክ ለመመስረት እንደሚፈልጉ ድምጽ የሰጡ ሲሆን በማግስቱም ከ700 ሺህ በላይ በባርሴሎና ጎዳናዎች ላይ በመሰለፍ ነጻነታቸውን እንደሚፈልጉ በመግለጽና የማድሪድን እና ጨካኝ የፓሊስ እርምጃኝ አውግዘው እንደነበረ ይታወቃል።

ዛሬ በባርሴሎና Catalan Civil Society (SCC) የካታሎኒያ ሲቪክ ማህብረሰብ አባላት በተጠራው መገንጠልን የመቃወም ሰልፍ ላይ እንደ አዘጋጆቹ አገላለጽ ከ930 ሺህ ህዝብ በላይ እንደተሳተፈበት ሲገልጹ የባርሴሎና ፓሊስ ሃይል ግን ቁጥሩን ከ360 ሺህ በላይ ሲል ዝቅ አድርጎታል።

የእስፓኝ ማእከላዊ መንግስት የተካሄደውን የመገንጠል ህዝበ ውሳኔ ህገ ወጥ በማለት ሲያወግዘው የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በበኩሉ ኢ-ሕገ መንግስታዊ ነው በማለት ፓሊስ የህዝበ ውሳኔውን የምርጫ ሂደት እንዲያስቆም ትእዛዝ እንደሰጠ ይታወሳል።

በፖሊስ በኩል ህዝበ ውሳኔውን ምርጫ ለማስቆም በወሰደው እርምጃ ዓለም አቀፍ ውግዘትን ያስከተለበትን የሃይል እርምጃ በመውሰድ ከ900 በላይ ሰዎችን ማቁሰሉ አይዘነጋም።
የዛሬው የካታሎኒያውያን ሰላማዊ ሰልፍ መገንጠልን በመቃወም ሲሆን ክስተቱ የማህበረሰቡን ለሁለት መከፈል የሚያሳይ ነው ተብሏል።