የህወሃት አመራር ፓርላማ እንደማይገኙ ታወቀ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የገዢው ኢህአዴግ ፓርቲ አስኳል [Hard Core] ህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት በመቀሌ እያካሄደ ባለው ልዩ ስብሰባ ምክንያት ነገ በሚከፈተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ መገኘት እንደማይችሉ ተሰማ።

በመቀሌ እየተካሄደ ያለው የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ልዩ ስብሰባ በኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ለመምከር ለ4 ቀናት የሚቆይ ስብሰባ መጀመሩን ይፋ ያደረገ ቢሆንም የተመደበለት 4 ቀን ተጠናቆ 6ኛ ቀኑን በያዘበት በዛሬው እለትም ድርጅቱ ስብሰባውን ባለማጠናቀቁ በነገው እለት ስብሰባው እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የህወሃት ድርጅት የገዢው ኢህአዴግ ፓርቲ አንደኛው ክንፍ ነው ተብሎ የሚገለጽበትን ሁኔታ በተጻረረ መልኩ መቀሌ ላይ በር ዘግቶ በወቅቱና በመጪው የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ እየመከርኩ ነው ማለቱ የተቀሩትን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በሀገር ጉዳይ ላይ ምንም ድርሻ የሌላቸው የህወሃት ስራ አስፈጻሚዎች መሆናቸውን በይፋ የገለጸበት ተግባሩ ነው ሲሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ።

አቶ ዓባይ ጸሃዬን ጨምሮ እንደ አቶ አስመላሽ የመሳሰሉት የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭ የሆኑት የመቀሌው ስብሰባ ታዳሚዎች በነገው የፓርላማ ጉባኤ ላይ ሊገኙ እንደማይችሉ ከስብሰባቸው ፕሮግራም መረዳት የተቻለ ሲሆን ለሁለት ወር በእረፍት ላይ የነበረው ፓርላማም የዚህን ዓመት ስራ ሀ-ብሎ ለመጀመር ነገ የሚከፈትበት ቀን መሆኑ ታውቋል።

ህወሃት መራሹ መንግስት በከፍተኛ ውስጣዊ ችግር የተተበተበ እንደሆነ እየተገለጸ ባለበት ሁኔታ የችግሩ ስፋትና ክብደት ከድርጅቱ አቅምና ብቃት በላይ በመሆኑ የሀገሪቷን ህልውና ለአደጋ አጋልጧል ሲሉ የህግና የፖለቲካ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በተለይም የገዢው ኢህአዴግ ፓርቲ ዋና አስኳል [Hard Core] በሆነው ህወሃት ድርጅት ውስጥ የተንሰራፋው ገደብ የለሽ ሙስና፣ /የመሬት፣ንብረትና ሀብት ዘረፋ/ ውስጣዊ የስልጣን ሽኩቻ እና ብቃትና ተሰሚነት ያለው መሪ መጥፋት በመንግስት ደረጃ እየተፈጸመ ላለው ሀገር አቀፍ ፖለቲካዊ ችግር ዋና መንስኤ ነው ሲሉ ታዛቢዎችና ምሁራን ደጋግመው የገለጹ ሲሆን ድርጅቱ ግላዊ ተሀድሶ እያለ በር ዘግቶ ከመመካር የዘለለ ፋይዳ ያለው ለውጥና መሻሻል ማሳየት የተሳነው ሆኖ ይገኛል።

የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ የመነጋገሪያ አጀንዳ የሀገር ጉዳይ ብሎ ለ4 ቀናት ለመምከር ተሰብስቦ ሰባትና ከዚያም በላይ ቀናት በር ዘግቶ መቀሌ ላይ ቢመክርም የወቅቱ ሀገር አቀፍ ፖለቲካዊ ቀውስ ዋና መንስኤ እራሱ እንደመሆኑ መጠን ከስብሰባው ተራማጅ የመፍትሄ አቅጣጫ ይመነጫል ብሎ መገመት መሲና ጊደር ትወልዳለች ብሎ እንደመጠበቅ ነው ሲሉ የስርዓቱን ውስጣዊ ሁኔታን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያ ይገልጻሉ።