የፌዴራሉ መንግስት የሶማሌን ክልል አስጠነቀቀ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የሶማሌ ክልላዊ መስተዳድር በተለይም በክልሉ ኮምኒኬሽን ቢሮ በኩል በየእለቱ እየተለቀቀ ያለው መግለጫ እጅግ አደገኛና ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ በማለት ከልሉ ከተግባሩ ይቆጠብ ሲል የፌዴራሉ መንግስት ኮምኒኬሽን ቢሮ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጠ።

የፌዴራሉ ኮምኒኬሽን ቢሮ ለሶማሊያ ክልል መስተዳድር በቀጥታ በላካው ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ከእንግዲህ መንግስት የሶማሌ ክልል እያካሄደ ካለው ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ቅስቀሳ ተግባሩ ካልታቀበ መንግስት የህዝቦችን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ መውሰድ ያለበትን እርምጃ ይወስዳል ሲል በጥብቅ ያስጠነቅቃል።
በዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የሚመራው የፌዴራሉ መንግስት ኮምኒኬሽን ቢሮ የሶማሌ ክልላዊ መስተዳድር በተለይም በአቶ ኢዲሪስ እስማኤል አንዲ የበላይነት የሚመራው የሶማሌ ክልላዊ መስተዳድር ህዝብ ግንኙነት ቢሮ ድረገጽና የማህበራዊ ሚዲያ በሆነው በፌስ ቡክ ገጽ ላይ የሚለቀቁት መልእክቶች እንዲቆሙ አዟል። የፌዴራሉ መንግስት ሁለቱም ክልሎች ሕዝብን ከህዝብ ከሚያጋጭና ከሚያነሳሳ ቀስቃሽ ተግባሮች እንዲታቀቡ ሲያጠነቅቅ፤ ድርጊቱ የተላለፈውን ግጭት ማብረጃ ህግ የተላለፈ ሆኖ እንዳገኘው እሁድ አመሻሹ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በሶማሌ ክልላዊ መስተዳድር ፕሬዚዳንት አብዲ ሞሀመድ ኦማር [ወይም አብዲ ኢሌ] እና በክልሉ ህዝብ ግንኙነት ቢሮ ሃላፊ አቶ ኢዲሪስ ኢስማኤል በኩል በኦሮሞና ሶማሌ ህዝቦች በኩል ከፍተኛ ግጭት የሚቀሰቅስና ለግጭት የሚያነሳሳ ክሶችና ፕሮፖጋንዳዎች በስፋት እያሰራጨ እንዳለ ይታወቃል።
የፌዴራሉ መንግስት በትናትናው ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያው በተለየ ሁኔታ ከሶማሌ ክልል በኩል በአቶ ኢዲሪስ እስማኤል የግል ፌስ ቡክና በመንግስታዊው የክልሉ ኮምኒኬሽን ቢሮ በኩል “The Oromo Peoples war against Ethiopian Somalis”፣ በኦሮሞ ሕዝብ በኢትዮጵያውያን ሶማሌዎች ላይ የተከፈተ ጦርነት በሚል ርእስ የወጣውን ጸብ ጫሪና ግጭት ቀስቃሽ ፕሮፖጋንዳን ለአብነት ጠቅሷል። የፌዴራሉ መንግስት በሁለቱ ክልሎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ባለበት ሰዓት ከሶማሌ መስተዳድር በኩል ይህን በተጻረረ እና አፍራሽ የሆነ እርምጃ ሲወሰድ ማየት መንግስት በትእግስት የሚያየው ጉዳይ አይደለም ሲል የጅጅጋውን መስተዳድር አስጠንቅቋል።

በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች መካከል በተነሳ ጦርነት ከሁለቱም በኩል በመቶ የሚቆጠር ሰው የተገደለ ሲሆን ከ150,000 በላይ በሶማሌ ክልል የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ሲባረሩ 392 በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የሶማሌ ተወላጆችም ከምስራቅ ኦሮሚያ መባረራቸው ተገልጿል።

ሁለቱም ክልሎች ለደረሰው ጥፋትና እልቂት የተጠያቂነትን ጣት አንዱ በአንዱ ላይ እየቀሰሩ ባሉበት ሂደት ከሶማሌ ክልላዊ መስተዳድር በኩል ለሳምንታት የዘለቀ ሃላፊነት የጎደለው መግለጫዎችና ትንኮሳዎች በተከታታይ በፕሬዚዳንቱና በኮምኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ በኩል ሲተላለፉ እንደነበረ ይታወቃል።

ከብዙ ዝምታና ቸልተኝነት በኋላ ከተኛበት እንደባነነ ሰው የፌዴራሉ መንግስት ኮምኒኬሽን ቢሮ የሶማሌ ክልል ፕሮፖጋንዳን አደገኛነት በመረዳት ለክልሉ መስተዳድር እጅግ ጠንከርና ጠበቅ ያለ ማስጠንቀቂያ ትናንት ማምሻውን ለማውጣት ችሏል።