በሊቢያ ስደተኞችን ሲያሰቃይ የነበረ ግለሰብ የጣሊያን ፍርድ ቤት የእድሜ ልክ እስራት በየነበት

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በሊቢያ በአፍሪቃውያን ስደተኞች ላይ ኢሰብአዊ ድርጊቶችንና ግድያ በመፈጸም ወንጀል የተከሰሰ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ደላላ ጥፋተኛነቱ ተረጋግጦ ፍርድ ተበየነበት።

በዜግነት ሶማሊያዊ የሆነው ኡስማን ማታሙድ በጣሊያን ሚላን ከተማ በዋለው ችሎት ስደተኞችን በመድፈር በማሰቃየት እና በመግደል ወንጀል የእድሜ ልክ እስራት ፍርድን ተከናንቧል።

የ22 አመቱ ኡስማን ማታሙድ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት እራሱን የተበደለ ስደተኛ እንደሆነ በማስመሰል በጣሊያን የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቁም ተዘግቧል።

በዚሁ ግለሰብ ዘግናኝ የሆኑ ድርጊቶች የተፈጸመባቸውና በሌሎች ሰዎች ላይ ይህ ድርጊት ሲፈጸም የተመለከቱ በጣሊያን የሚገኙ የሶማሊ ስደተኞች ለፖሊስ ባደረጉት ጥቆማ ኡስማን ማታሙድ በሴፕተምበር 2016 እኤአ በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉ ይታወሳል።

በፍርዱ ሂደት በጠቅላላው 17 የሚደርሱ ስደተኞች በዚህ ግለሰብ የተፈጸመባቸውን ግፍ፣ አስገድዶ መድፈር፣ እስር እና ስቃይ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ እንደሚቃወምና የተዘረዘሩትን ወንጀሎች እንዳልፈጸመ ሲናገር፤ ጠበቃው በበኩላቸው ተከሳሹ ይግባኝ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

አስቸጋሪውን የሰሃራ በረሃ በማቋረጥ የሜዲትራኒያን ባህር እጅግ አደገኛ በሆነ መልኩ በመሻገር በአውሮፓ ጥገኝነትን የሚጠይቁ አፍሪቃውያን ስደተኞች በደላሎች የሚደርስባቸውን ኢሰብአዊ ድርጊቶች ለማመን የሚያዳግቱ እንደሆኑ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች በሪፖርታቸው ሲያቀርቡ ቆይተዋል።