የዶላር ዋጋ በባንክ 27 ብር በጥቁር ገበያ 33 ብር ገባ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሐገሪቱን የብር የምንዛሪ ዋጋ ከሰባት ዓመት በኋላ ለመቀነስ በመገደዱ ዛሬ በአስራ-አምስት ከመቶ መቀነሱን ከሮይተርስ ዜና ዘገባ ማወቅ ተችሏል፡

ብሔራዊ ባንኩ የብር ምንዝሪን ዋጋ ለመቀነስ የተገደደበት ዋና ምክንያት የንግዱን እንቅስቃሴ ለማበረታታት እንደሆነ የገለጸ ቢሆንም የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ግን የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የፈጠረው ተጽእኖ ውጤት ነው ካሉ በኋላ የእጥረቱ ምንጭም ሀገሪቱ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ምርት መቀነስ ተክትሎ የመጣ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተነሳው ሀገር አቀፍ ህዝባዊ ዓመጽ እየተናጠች ያለች ሀገር ስትሆን ሂደቱ የሀገሪቷን በተለይም መንግስት መር የሆነውን ኢኮኖሚ ክፉኛ ማንኮታኮቱ ይታወቃል።

ትናንትና በተከፈተው የኢትዮጵያ ፓላማ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላት ተሾመ መንግስት የብርን ዋጋ ማሻሻያ እርምጃ ይወስዳል በማለት የገለጹ ሲሆን መንግስታቸው በደረሰበት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት በያዝነው በ2010 ዓ.ም ሊሰሩ ከታቀዱት እንደ የባቡር ሓዲድ ግንባታና የመሳሰሉት ግዙፍ ግንባታዎች እንደማይካሄዱ መግለጻቸው ይታወቃል።

በአዲሱ የዋጋ ተመን መሠረት አንድ የአሜሪካን ዶላር ወደ 27 የኢትዮጵያ ብር ገደማ የሚመነዘር ሲሆን ይህም የብር ዋጋ በ15% እንደወረደና የዶላር ዋጋ እንደጨመረ ያሳያል። ከሰባት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢትዮጵያን ብር ዋጋ በ17 በመቶ ከፍ በሚያደርግ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ማስተዋወቁ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ በአሁኑ የብር ዋጋ ተመን መቀነስ ምክንያት ወደ ሐገር በሚገቡ ሸቆጦች ላይ የዋጋ ንረት እንደሚያስከትል፣ ወደ ውጭ በሚላካው የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የሚኖረዉ አስተዋፅኦ እድሜ የለሽ አጭር ግዜ ያህል መጠነኛ ውጤት እንደሚያመጣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ከዚሁ የብር ዋጋ ተመን መቀነስ ዜና ሳንወጣ፤ ከአዲስ አበባ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው አንድ የአሜሪካን ዶላር በጥቁር ገበያ በ33 ብር ዋጋ እየተገዛ ሲሆን ብሔራዊ ባንኩ ደግሞ አንድ የኩዌት ዲናርን በ87 ብር ዋጋ እንዲመነዘር መደነገጉን ለማወቅ ተችሏል።