የኬኒያው ተቃዋሚ ከፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እራሱን አገለለ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ታዋቂው የኬኒያ ተቃዋሚዎች ሕብረት ናሳ [National Supper Alliance] መሪ እና በባለፈው ነሃሴ 8 ቀን ፕሬዚዳንታዊ እጩ ተወዳዳሪ የሆኑት አቶ ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ በያዝነው ወር ጥቅምት 26 ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እራሳቸውን ማግለላቸውን ዛሬ ይፋ አደረጉ።

የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ ዛሬ እንዳስታወቁት እራሳቸውን ከውድድሩ ያገለሉት የሐገሪቱ አስመራጭ ኮሚሽን እና የምርጫ ሥርዓት እንዲስተካከል ያቀረቡትን ባለ 11 ነጥብ ጥያቄዎችን በተገቢ ሁኔታ መልስ ሊያገኝ ባለመቻሉ እና ብሎም የምርጫውን ሂደት ባጭበረበረው የምርጫ ቦርድ ባለስልጣናት ስር ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንደማይገኙ በመግለጽ ከውድድሩ እራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል።

ባለፈው ነሀሴ 8 ቀን 2017 በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በስልጣን ላይ ያሉትን ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን አሸናፊ አድርጎ ቢያውጅም አቶ ራይላ ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት ወደ ፍርድ ቤት በመሄዳቸው የሀገሪቱ ጠ/ይ ፍርድ ቤት የምርጫውን ውጤት ውድቅ በማድረግ ድጋሚ ምርጫ በ60 ቀናት ግዜ ገደብ ውስጥ እንዲካሄድ በመወሰኑ 2ኛው ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በጥቅምት 26 ቀን 2017 እንዲካሄድ ተወስኖ በዝግጅት ላይ እንዳሉ ይታወቃል።

ዛሬ ኬኒያውያን በሁለት ተከፍለው ሲከራከሩ ውለዋል። ገዢው የኢዩቤሊዩ ፓርቲ የወሰነውን ውሳኔ ገና ያላሳወቀ ሲሆን የምርጫ ቦርድ ኮሚሽንም ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ አዲስ አቅጣጫ ጠቋሚ ትእዛዝ ውሳኔ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

የተቃዋሚው ናሳ ጥምር ሃይል የምርጫ ቦርድ ኮሚሽን እንዲያስተካክል ያቀረብኩት ባለ 11 ነጥብ ጥያቄዎች ካልመለሰ በምርጫው አለመሳታፍ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ውስጥ ምርጫው እንዳይካሄድ አግዳለሁ ማለቱ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረትም ኬኒያ ወደ ሕገ-መንግስታዊ ቀውስ እያመራች ያለች ሀገር ሆናለች።