የቴዎድሮስ ራእይ ተውኔት የአውሮፓ ጉብኝቱን (ቱሩን) በጀርመን ኑረንበርግ ከተማ አጠናቀቀ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በተለያዩ የዩናይትድ ስቴትስ ከተሞች ለህዝብ ሲቀርብ የነበረው የቴዎድሮስ ራእይ ተውኔት በአውሮፓም ጉዞውን በተሳካ መልኩ ሲያደርግ ቆይቷል።

ጣይቱ የባህልና የትምህርት ማእከል ታዋቂ አርቲስቶችን ከኢትዮጵያ ድርስ በማስመጣትና ከተለያዩ የአለማት ክፍል የሚገኙትንም በማሰባሰብ በተሳካ መልኩ በአውሮፓ ይህን የቴዌድሮስ ራእይ ተውኔትን ለህዝብ ለማቅረብ ችሏል።

11

በአንጋፋዋና ታዎቂዋ አርቲስት አለምጸሃይ ወዳጆ በበላይነት የሚመራው የጣይቱ የባህልና የትምህርት ተቋም በውጭ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ታሪክህን እወቅ በሚል መርህ ይህንን ዘመን ተሻጋሪውን የቴዎድሮስ ራእይ ቲያትርን ለማዳረስ ጥረት አድርጓል።

የአርቲስቶችን ወጪ፣ መስተንግዶ፣ የበረራ ትራንስፖርት እንዲሁም ማረፊያ በሙሉ ሃላፊነት በመሸከም ኢትዮጵያውያን በሚገኙበት የአውሮፓ አገራት በመዘዋወር የአንድነት ታሪካችንን ወደ ኋላ መለስ ብለን እንድናይና ለዛሬው መመሰቃቀላችን መፍትሄ ማበጃም እንዲሆን የጣይቱ የባህልና የትምህርት ተቋም ያደረገው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነበር።

አርቲስት አለምጸሃይ ወዳጆ በውስጧ ሁሌም የሚነደው የአገር ፍቅር ስሜቷ እንዲሁም የኪነጥበብ ፍላጎቷ አስገድዷት በተለያዩ የሰሜን አሜሪካና የአውሮፓ ከተሞች አድካሚ በሆነ መልኩ በመዘዋወር የቴዎድሮስ ራእይ ተውኔትን ለኢትዮጵያውያን ለማዳረስ ችላለች።

በጀርመን ዋና ከተማ በበርሊን፣ የፋይናንስና ባንክ ሃብ በሆነችው ፍራንክፈርት እንዲሁም በኑረንበርግ ከተሞች የጣይቱ የባህልና የትምህርት ማእከል የቴዎድሮስ ራእይ ቲያትርን ለህዝብ እይታ በተሳካ መልኩ አቅርቧል።

የቴዎድሮስ ራእይ ተውኔት በጥቅምት 8 ቀን 2017 እኤአ በጀርመን ኑረንበርግ ከተማ ለህዝብ ቀርቦ የአውሮፓ ጉብኝቱንን ወይም ቱሩን በታላቅ ስኬት ለማጠናቀቅ በቅቷል።

በኑረንበርግ ከተማ ከ500 በላይ ታዳሚዎች የአዳራሹን መቀመጫዎች ሞልተው ከዚህ በኋላ በአውሮፓ ዳግም አናገኘውም ያሉ በርካታ ታዳሚዎች ደግሞ ቆመው ቲያትሩን ተከታትለዋል።

     

በሙኒክ ከተማ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንም ይህን ቲያትር ለመታደም ከሁለት ሰአታት በላይ በመንዳት በኑርነንበርግ ከተማ መገኘታቸውን ለአባይ ሚዲያ ገልጸዋል።

ቲያትሩን ሲከታተሉ የነበሩ ኢትዮጵያውያን አንዳንዴ በቁጭት አለፍ ብሎም በሃዘን ከዚህም በላይ ከአጼ ቴድሮስ፣ ከተዋበች እንዲሁም ከገብርዬ በሚወጡ የጀግንነት ቃላት እየተደነቁ በጭብጨባና በፉጨት ስሜታቸውን ሲገልጹ ተስተውሏል።

ተመልካቾች ቲያትሩን በአስደናቂ ሁኔታ ከተጫወቱት ተዋንያን ጋራ የማስታወሻ ፎቶዎች ሲነሱና አድናቆታቸውን ከቃላት አልፈው በስጦታ ሲገልጹም ታይተዋል።

ለ17 አመታት በቆራጥነት ለኢትዮጵያ አንድነት በኪነጥበቡ ዘርፍ እየታገለች ላለችው የጣይቱ የባህልና የትምህርት ማእከል መስራች እንዲሁም ሊቀመንበር አርቲስት አለምጸሃይ ወዳጆ የቲያትሩ ታዳሚዎች ከመቀመጫቸው በመነሳት ያላቸውን ክብርና ምስጋና ገልጸውላታል።

ከዚህም በተጨማሪ እያደረገች ላለችው አገርን የማዳን፣ አንድነትን የማጎልበት እንዲሁም ኢትዮጵያዊነትን የማራመድ የጀግነት ተግባር መላው ታዳሚ ረዘም ላለ ደቂቃዎች በመቆምና በማጨብጨብ አድናቆቱን ለግሷታል።

አንጋፋዋ አርቲስት አለምጸሃይ ወዳጆ በጣይቱ የባህልና የትምህርት ማእከል በኩል በርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው እንዲሻሻል ከተለያዩ የውጭ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመጻጻፍ የነጻ የትምህርት እድል ወይም ስኮላርሺፕ እንዲያገኙ የምታደርገው አኩሪና ቅዱስ ተግባር ከምንም በላይ የታዳሚውን ልብ ማርኮታል። 

በኑረንበርግ የኢትዮጵያውያን የባህል ኮሚኒቲ ኪነጥበቡን ከማስፋፋት በተጓዳኝ የበርካታ ኢትዮጵያውያንን የህይወት ጎዳና እንደዚህ ባለ የነጻ የትምህርት እድል እንዲስተካከል ከአስር አመታት በላይ እየተንቀሳቀሰ ላለው የጣይቱ የባህልና የትምህርት ማእከል የማበረታቻና የምስክር ሽልማት አበርክቷል።

ኢትዮጵያን በጥበብና በስልጣኔ ለማራመድ ራእይ ሰንቆ የተነሳው ታላቁ መሪ አጼ ቴዌድሮስ ምንም እንኳን ራእዩ ባይሳካም፤ የጣይቱ የባህልና የትምህርት ማእከል በርካታ ኢትዮጵያውያን ጥበብንና እውቀትን እንዲያገኙ የሚያደርገው ተግባር በርግጥም የቴዎድሮስን ራእይ ለመፈጸም ነፍሱን ከሰጠው ከገብርዬ ውለታ ሊተናነስ የማይችል እንደሆነ በመገመት ይህን ማእከል መደገፍ የሁላችንም የዜግነት ድርሻ መሆን አለበት ሲሉ ያነጋገርናቸው ታዳሚዎች ገልጸውልናል።