የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት መላቀቅ አልቻሉም ተባለ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ባለፈው ሳምንት ሰኞ እለት በመቀሌ የተጀመረው ልዩ የህወሃት ማእከላዊ ኮሜቴ አባላት ስብሰባ ከሰባት ቀናት ዝግ ሰብሰባ በኋላ ትናንት በሰባተኛው ቀን ስብሰባው መጠናቀቁን ድርጅቱ በገለጸ ማግስት ማክሰኞም እየተካሄደ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የገዢው ኢህአዴግ ፓርቲ አስኳል [Hard Core] የሆነው የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ልዩ ስብሰባ ለአራት ቀን ተብሎ የተጀመረ ሲሆን በስድስት ዋና ዋና የመወያያ አጀንዳዎች ላይ ለመነጋገር እቅድ እንደያዘ ተገልጾ ሰባት ቀን ከፈጀ ስብሰባው በኋላ ሁለቱን አጀንዳዎች ብቻ ማጠናቀቅ መቻሉን ኢሳት ገልጿል።

በተቀሩት አራት አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት የስብሰባው መቀጠል አስፈላጊነትና ረዥም ቀናት ሊፈጅ እንደሚችል በመረዳት የስብስባውን ፍጻሜ አብስረው በፌዴራሉ ውስጥ ሃላፊነት ያለባቸውን ወደ አዲስ አባባ በመላክ የተቀረውን አራት አጀንዳ በቀሪዎቹ የድርጅቱ አመራር አባላት ስብሰባው እንዲቀጥል ተወስኗል ሲሉ ምንጮቻችን ገልጸውልናል።

3ኛ ዓመት የስራ ዘመኑን ሰኞ እለት የጀመረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች የህወሃት ተወካዮች መገኘት ግዴታ ስለሆነ ድርጅቱ [ህወሃት] የተወሰኑትን አመራር ወደ አዲስ አበባ ለመላክ እንደተገደደ ነው የምንጮቻችን መረጃ የሚያመለክተው።

የማእከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ በ4 ቀናት ውስጥ በስድስት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ሊያሳልፍ እንደተዘጋጀ የተገለጸ ሆኖ ሳለ ከሰባት ቀናት በኋላ ከ6ቱ የመነጋገሪያ አጀንዳዎች ውስጥ ሁለቱ ብቻ መጠናቀቅ መቻሉ የተሰብሳቢዎቹን በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ የከረረ ክርክር መፍጠር ምክንያት እንደሆነ የሚገልጽ ማስረጃ ነው ሲሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ።

በህወሃት መራሹ መንግስት አገዛዝ ስር ባለችው በዛሬይቷ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፈታኝ ችግሮች የሀገሪቷን ህልውና እየተፈታተነ ያለበት ወቅት ነው። የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ እንደሆነ በስፋት እየተገለጸ ያለው የስርዓቱ አስኳል [Hard Core] የሆነው የህወሃት አመራርና ድርጅቱ በኪራይ ሰብሳቢነት፣ በገደብ የለሽ የሙስና ተግባር፣ በስልጣን ያለአግባብ መጠቀምና መባለግ፣ በቋንቋ ተኮር እርምጃና በብቃት ማነስ ችግሮች የተጥለቀለቀ ሆኖ መገኘት ነው በማለት ታዛቢዎች ይገልጻሉ።

እንደታዛቢዎቹ አባባል በተጠላለፈና በተወሳሳበ ውስጣዊ ችግሮች ተይዞ የመበስበስ ሁኔታ ላይ ያለው ህወሃት ችግሮቼን በተሃድሶ እፈታለሁ እያለ ደጋግሞ ተሃድሶ መግባቱን ቢገልጽም ተሃድሶ አድርጌያለሁ ከሚለው መግለጫው ባሻገር ያሳየው ለውጥም ሆነ መሻሻል ስለሌለ፣ ከመቀሌው የተራዘመ ስብሰባ ለኢትዮጵያ የተሻለ እርምጃ መጠበቅ አይቻልም ሲሉ ይገልጻሉ።