ፕ/ር መረራ ጉዲና ይቅርታ አልጠይቅም ማለታቸው ተሰማ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ባለፈው ዓመት በአውሮፓ ህብረት ጋባዥነት በብራስልስ ተገኝተው ስለኢትዮጵያ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተው ሲመለሱ የታሰሩት ፕ/ር መረራ ጉዲና ከእስር ለመፈታት ብለው መንግስትን ይቅርታ እንደማይጠይቁ መግለጻቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ምንጮቻችን እንደገለጹት ባለፈው ሳምንት ፕ/ር መረራ ጉዲን ባሉበት ቃሊቲ እስር ቤት ከመንግስት በተላኩ አራት ሽማግሌዎች የተጎበኙ ሲሆን የጉብኙቱም አላማ ሽማግሌዎቹ በእስር እየማቃቁ ያሉትን ፕ/ር ከመንግስት ጋር አስታርቀው ለማስፈታት እንደነበረ ተነግሯል።

ፕ/ር መረራ ጉዲና ከብራስልስ መልስ ያሰራቸው የመንግስት ደህንነት ክፍል ቆየት ብሎ በአቃቤ ህግ በኩል ፕ/ሩን በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ መስርቶባቸው ቃላቲ እንዳስገባቸው ይታወቃል። ፍርድ ቤት የተነበበላቸው ክስ በፌዴራሉ መንግስት ፓርላማ በአሸባሪነት ከተፈረጀው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅት መሪ ከሆኑት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ተገናኝተሃል የሚል እንደሆነ ታውቋል።

በአቃቤ ህግ በኩል በፕ/ር መረራ ጉዲና ላይ የተከፈተው ከአሸባሪዎች ጋር ተገናኝተሃል ክስ ውስጥ ፕ/ሩን በኦሮሚያና በተቀሩት የሀገሪቱ ክፍል ውስጥ ለተነሳው ህዝባዊ እምቢተኝነት ተጠያቂ በማድረግ ፕ/ሩ ከሀገር ውጪ ካሉት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋና የኦሮሞ አክቲቪስቱ ጁሃር መሀመድ ጋር መንግስትን እና ሕገ መንግስቱን በሃይል ለማፍረስ ሙከራ ክስ መስርቶባቸው በእስር እየተንገላቱ ያሉ ምሁር እንደሆኑ ይታወቃል።
በሀገር ውስጥና በውጭ ሃይሎች በተለይም በአውሮፓ ህብረት መንግስት ፕ/ሩን በአስቸካይ እንዲለቅ የሚያሳስብ ተከታታይ ጥሪዎች እና ጥያቄዎች ሲቀርቡለት እንደነበረ ይታወቃል። ባለፈው ሳምንት መንግስት ሽማግሌዎቹን ወደ ቃሊቲ በመላክ ፕ/ሩን አግባብተውና ይቅርታ እንዲጠይቁ በማድረግ ሊፈታቸው መወሰኑን ነው ከሽማግሌዎቹ ጉብኝት መረዳት የተቻለው። ሆኖም ፕ/ር መረራ ጉዲና በመንግስት በተላኩባቸው ሽማግሌዎች በኩል የቀረበላቸውን የይቅርታ ጠይቁና ከእስር ይፈቱ ጥያቄን ባለመቀበል ይቅርታ የምጠይቅበት ጥፋት አልፈጸምኩም በሚል የጸና አቋም ሽማግሌዎቹን እንደመለሳቸው ነው መረዳት የተቻለው።

የአውሮፓ ህብረት፣ ተመድ፣ አሜሪካ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ፕ/ር መረራ ጉዲና የህሊና እስረኛ እንጂ የወንጀል እስረኛ አይደሉም በማለት መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊፈታቸው ይገባል በማለት ለመንግስት ተደጋጋሚ ጥያቄን እያቀረቡ ባለበት ሁኔታ የፕ/ሩ ያለጥፋትና ወንጀል መታሰርን በመቃወም በመላ ኦሮሚያ ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞ፣ ሰልፍና የስራ ማቆም አድማ ሲያደርጉ እንደነበረ አይዘነጋም።

መንግስት በሀገር ውስጥና በውጭ በተነሳበት ተጽእኖ ፕ/ሩን ለመልቀቅ በ1999 ዓ.ም የቅንጅት መሪዎችን ከእስር በለቀቀበት ስልት የጥፋተኝነትና ይቅርታ ፎርም አዘጋጅቶ እንዲፈርሙ የፈለገ ቢሆንም የፕ/ሩን ይሁንታ ሊያገኝ እንዳልቻለ መረዳት ተችሏል።