አባዱላ ገመዳ የእኛ አጀንዳ (በይገረም አለሙ)

0

አምና በዚህን ሰአት፣ ልክ አንደ ሰሞኑ ፓርላማው ሲከፈት ፕሬዝዳንት ሙላቱ አንብቡ ተብሎ የሚሰጣቸውን ይዘው ፣ከፓርላማ ተገኝተው የምርጫ ህጉን እስከ መሻሻል ሄደን ከተቀዋሚዎች ጋር  አብረን  እንሰራለን  አሉ፡፡ ተቃውሞአችው እንደ ዥዋዥዌ ጨዋታ የሆነው አንዳንዶች በዚህ ንግግር ተመስጠው እውነት አድርገውም ወስደው ወያኔ ከመቅጽበት የተፈጥሮ ባህሪውን ይለወጥ ይመሰል አምነውት ሊያሳምኑን ባይሳካላቸውም ትንሽ መንገድ ተንገዳገዱ፡፡ ይሄው ዛሬ አመቱ ላይ ቆመን መለስ ብለን ስንቃኝ በፕሬዝዳንቱ ከተነገረውና የአንዳንዶችን ቀልብ ካማለለው አንዱም ገቢራዊ አልሆነም፡፡ ለወያኔ ግን አልጠቀመውም ለማለት አይቻልም፣ በተለይ በውጪ ግንኙነት ረገድ ብዙ ፕሮፓጋንዳም ሰርቶበታል፡፡   የአንዳንዶቹን ተቀዋሚዎች ነገረ ሥራ በጥሞና ላስተዋለው ሞኝ ቀበሮ  የበሬ ምን ይውድቅልኛል ብላ  አንጋጣ ስትከተል  ትውላለች የተባለውን ይመስላል፡፡ከመድረኩ ጠፍተው ከነመኖራቸውም ተረስተው የሆነ ነገር ተፈጥሮ የፖለቲካው አየር ሲሟሟቅ  የሥልጣኑ መንገድ ወለል ያለ ይመስላቸውና  አለን ከማለት አልፈው ሽቅደድም ይጀምራሉ፡፡

ዘንድሮ  ደግሞ በፕሬዝዳንቱ የሚነገረው ውሸት አለቀ ወይንም የተበላ ሆነና ከእንግዲህ ማንንም ሊያማልል አይችልም ተብሎ ታመነ መሰለኝ  በፓርላማው መክፈቻ ዋዜማ የአባ ዱላ መልቀቅ ወሬ ሆኖ ለእኛ ማጫወቻና መሻኮቻ ተለቀቀልን፡፡ ወያኔ ስነ ልቦናችን ገብቶት የደም ዝውውራችንን ከፍታ ዝቅታ በሚገባ ማወቅ ችሎ በየግዜው እየመጠነ ሲለው መጫወቻ ሲለው መጮሂያ ሲፈልግም ርስ በእርስ መናጫ አጀንዳ እየወረወረ ይጫወትብናል ያጫውተናል፡፡ መቼም በምንምና ከምንም የማይማሩ ከንቱዎች ሲገኙ መርገጥ ነው አንጂ አጀንዳ እየቀያየሩ የምን ብሄራዊ መግባባት የምን የህግ በላይነት፡፡

 ከራስ ጋር መቃረን፡፡

አባ ዱላ በወያኔ ፈቃድና ስሪት በአንድ ጀንበር ጀነራል  አድርጎ የጦር አዛዥ ሲሻው ደግሞ በአንድ ጀንበር  ወደ አቶነት አውርዶ  የክልል ፕሬዝዳንት በዚህ ረገድ አገልግሎቱ ሲያበቃ ደግሞ ለጡረታ ይሁን ለቅርብ ክትትል ባይታወቅም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚባለው የፌዝ መድረክ አፈ ጉባኤ በማድረግ  ሲጫወትበትና ሲያጫውተው የኖረ ሰው በመሆኑ ብዙዎች የወያኔ አሻንጉሊት ነው በራሱ ምንም ማድረግ አይደለም መነጋር የማይችል ሰው ነው ስንለው ኖረናል፡፡

እንዲያ ስንለው የኖርነው ሰው ዛሬ መቀጠል የማልችልበት ሁኔታ ስለተፈጠረ ልቀቁኝ አለ ብለን  የእሱን መልቀቅ አንደ ትልቅ ነገር ቆጥረን አጀንዳችን ስናደርግ ለእኔ ከራስ ጋር መቃረን ሆኖ ይታየኛል፡፡ አሻንጉሊት ነው የተባለ ሰው በኃላፊነቴ ለመቀጠል የማያስችል ሁኔታ ስላጋጠመኝ ስላለ እንዳውም ይህን ለማድረግ የበቃው  እንዴት  በማንና በምን ሁኔታ እንደሆነ ገና ባልታወቀበት ሁኔታ እሱን አጀንዳ ማድረግ ነገሮች ምን ያህል በስሜት እንደሚጦዙ ማሳያ ነው፡፡ ለእኔ የአባዱላ ጉዳይ ወደ ፊት የምንሰማው ተጠባቂ ሆኖ አበው ተለበሰ ቀረ የደበሎ ቅዳጅ እንደሚሉት ነው፡፡  

ምንም አይፈይድም በወያኔ ሳንባ የሚተነፍስ ግዑዝ ነገር ነው ስንለው የባጀነው ሰው መቀጠል አልችልም ማለቱን ተከትሎ ከሚጻፉና ከሚነገሩ ነገሮች አንዱ  የእሱ መልቀቅ በወያኔ ሰፈር በህውኃት ሰፈር መደናገጥን በኦህዴድ ሰፈር መነሳሳትን አንደሚያመጣ ተደርጎ የሚገለጸው ነው፡፡

በወያኔ ሰፈር አይደለም አንድ ያውም ምንም የማድረግ  የመናገር አቅም የሌለው ተከላሽቶ የተቀመጠ ሰው ቀርቶ ( የአባዱላ መኮላሸት ከምርኮኛነት ወደ ኦህዴድ መስራችነትና አመራር ባልት በተቀየረበት ግዜ ነው የሚጀምረው፤ከቤትህና ከድርጅትህ ምረጥ ተብሎ ቤቱን ለድርጅቱ ማውረሱንም ማስታወስ ያስፈልጋል፣ አፈ ጉባኤ የሆነውም በመለስ ትዕዛዝ እንጂ በእርሱ ፍላጎት እንዳልነበረ ጸሀይ የሞቀው ሀቅ ነው)  ጦርነትን ማሸነፍ ብቻ አይደለም መስራትም እንችላለን እያሉ ይመጻደቁ የነበሩት እነ አቶ ስዬም በእኩል ቁጥር ከህውት ተለይተው የተፈጠረ ነገር የለም፡፡

 በኦህዴድ ሰፈር መነሳሳት የሚባለውም ቢሆን ይህን ያህል አመት ወገኖቹ በወያኔ ወታደሮች ሲገደሉ ታፍሰው ታስረው ሲሰቃዩ ቅንጣት ያልተሰማው ሰው ዛሬ የአባዱላ መልቀቅ መንፈሱን ያነሳሳዋል፣ ለእምቢታ ይቀሰቅሰዋል ማለት ራስን ማታለል ነው፡፡  ያውም አባዱላ እለቃለሁ ያለበት ምክንያት ገና ባልታወቀበትና ባላለቀበት ሁኔታ፡፡ ታምራት ላይኔን እዚህ ጋር ማስታወስ ያስፈልግ ይሆን!

ኦህዴዶች ከዚህ ተምረው ከጥፋት ሊመለሱ ከወያኔ አሽከርነትም ራሳቸውን ነጻ ሊያወጡ ይችላሉ ከሚለው ይልቅ በአባ ዱላ ላይ ሊዘምቱ ይችላሉ የሚለው ግምት ለእውነት የቀረበ ይሆናል፡፡ ወያኔ እሾህን በእሾህ ስልትን በሚገባ የተካነበት በመሆኑ፡

ለውጥ የሚመጣው በወያኔ ድክመት ሳይሆን በተቀዋሚው ጥንካሬ ነው፡፡

ወያኔ  ከመንበረ ሥልጣኑ ሊሸኝ ይበቃ የነበረባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አልፈዋል፡፡ ቢያንስ የ1992 ክፍፍል እና የ1997 የምርጫ ሽንፈት የቅርብ ግዜ ትዝዎች ናቸውና  ሊረሱ አይችሉም፡፡ የ2008ቱ ህዝባዊ አመጽም ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ወያኔ ውስጥ አንድ ነገር ሲፈጠርም ሆነ ህዝቡ ብሶቱ ብሶ ጠመንጃን  መጋፈጥ ሲጀምር ተቀዋሚው የሚባለው ወገን ያንን አጋጣሚ እንዴት ሊጠቀምበትና ወደ ሀገራዊ ለውጥ ሊለውጠው እንደሚችል  ማሰብና መምከርና መስራት ሲገባው ይህ  እስከ ዛሬም አልታየ ዛሬም ያለ አይመስልም፡፡ ይህ በመሆኑም ነው ወያኔ በሁለት እግሩ ቆሞ ብቻ ሳይሆን እየተንገዳገደ በምርኩዝ ተደግፎም ሆነ ከዛ ብሶ አጎንብሶ እየሄደ ጭምር ቀጥቅጦ የሚገዛን፡፡ስለሆነም ወያኔ ሰፈር የሚፈጠር ነገርን ከማራገብ ስለ ራስ ጎራ ጥንካሬ ማሰብ ይበል ጠቀሜታ አለው፡፡  

ተቀዋሚው ባብዛኛው በየራሹ ጎጆ መሽጎ  አይጥና ድመት በሆነበት፣ መተባበሩ ቀርቶ መከባበሩ አልሆን ባለበት፣ ሌላው ሁሉ ቢቀር አንተም በመንገድህ እኔም በመንገዴ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ መባባል ሲገባ በተቃራኒው አንዱ የሌላኛው እንቅፋት ለመሆን በሚንደፋደፍበት ሁኔታ ወዘተ አይደለም አባ ዱላ ገመዳ ኃይለማሪያምም መቀጠል አልችልም ብሎ ቢሰናበት የሚመጣ ሀገራዊ ለውጥ የለም፡፡ በተቃዋሚው ጎራ ሁኔታ ቁልፍ የምንላቸው ወያኔዎች በሙሉ እንኳን ከሥልጣኑ ሰፈር ገለል ቢሉ ከሎሌዎቹ መካከል የተሻለው ሎሌ ከፊት እየቀደመ ይገዛናል እንጂ የሚለወጥ ነገር አይኖርም፡፡

ስለሆነም በወያኔ ሰፈር በሚፈጠር የግለሰቦች መልቀቅም ሆነ ክፍፍልና መሻኮትም ሆነ በየኤምባሲ በሚደረግ ሰልፍና ጩኸት ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል ለመረዳት ሀያ ስድስት ኣመት ከበቂ በላይ ነውና የተለየ ጥናትም ሆነ ውይይት የሚያሻው አይደለም፡፡

አዲስ አመት ከመድረሱ ሶስት ወራት አስቀደሞ  ለአዲስ ዓመት ቅድመ ዝግጅት- በራሳችን ላይ እንዝመት በሚል ርዕስ ሀሳቤን አጋርቼ ነበር፡፡ እንዲህ ብዬ ነበር ማለቱን ብዙም ባልወደውም ሁኔታዎች ግድ የሚሉበት አጋጣሚ ይፈጠራልና ያላባራ ጩኸት አንድ ቀን ሰሚ ሊያገኝ ይችላልምና  አምስት ወራት ከሆነው ሰሚ ያጣ ጩኸት ውስጥ አንድ አንቀጽ ወስጂ ለማሳረጊያነት መጠቀም ዳዳኝ፡፡

ሀያ ስድስት ዓመት ሙሉ ከወያኔ ጋር ያለውን ገመድ ጉተታ ትተን እርስ በእር እየተጓተትን ወጥረን ተወጣጥረን ወያኔ እየተንገዳገደም ወድቆ እየተነሳም እንዲገዛ አበቃነው፡፡ ይህ ሊቆጨን ሲገባ ፈጽሞ ስሜት አልሰጠንምና፡አሁንም  እዛው የዛሬ ምናምን አመት በቆምንብት ነን፡፡ እንው እስቲ በእኛ በቀጥታ ባይደርስብንም በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ላይ የሚፈጸመው ሞት እስራት ስደት እንግልት ይታሰበንና የሀገሪቱ በጥቂቶች መቦጥቦጥ ይቁጨንና አዲሱ አመት ከመድረሱ አስቀድሞ ባሉት ሶስት ወራቶች የጠጠረውን ትተን የላላውን የምንወጥርበት፣ የትም ሊያደርሰን ካልቻለው መንገድ ወጥተን አዲስ መንገድ የምንመርጥበት፣ የአስተሳሰብ ለውጥ አድርገን ከራስ በላይ ሀገር ለማለት የምንበቃበት፣ዙፋኑ አንድ ብቻ መሆኑንና እርሱም በህዝብ ፈቃድ መያዝ የሚገባው መሆኑን በማመን በየኪሳችን ያለውን ዘውድ ለመጣል ቢያሳሳንም በየቁም ሳጥናችን ውስጥ የምንቆልፍበት  ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያስችለን ዘመቻ በየራሳችን  ላይ ላይ እናውጅ፡፡

ትውስታ ውስጥ ስገባ ሌላም ነገር ትውስ አለኝ፡በመነሻየ ላይ የጠቀስኩት የዛሬ አመቱ የፕሬዝዳንቱ ንግግር በተደመጠ ማግስት ፕሬዝዳንቱም ሆኑ እሳቸውን ተከትሎ በዛው ሳምንት ተናገሩት ጠቅላይ ምኒስትር በንግግራቸው ህገ መንግሥቱን አንደማያውቁት በገሀድ አሳይተው ነበርና ፕሬዝዳንቱም ጠቅላይ ምኒስርትም የማያውቁት ህገ መንግስት በሚል ርዕስ ጽፌ ነበር፣ አዛ ጽሁፍ ውስጥም የዛሬው መልእክቴ አዲስ እንዳልሆነና አንድ ቀን በማለት ደጋግሜ የተመላለስኩበት መሆኑን የሚያሳይ አንድ አንቀጽ እንዲህ ይላል፡፡

ስለሆነም የምርጫ ህግ ማሻሻያ ዲስኩሩ  ከፕሮፓጋንዳ አልፎ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አይደለምና ከወያኔም ባህርይ ሥልጣንን የማጥበቅ አንጂ ከሕዝብ የመታረቅ ተግባር አይጠበቅምና፣ ለመሰረታዊ ለውጥ ሳይሆን ለእድሜ ማራዘሚያ ለተግባራዊነት ሳይሆን ለማደናገሪያና ለማስቀየሻ ከወያኔ ሰፈር በሚነገሩ ጉዳዮች አለመዘናጋት የነጻነቱን ቀን ለማቀረብ ይበጃል፡