በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገደሉት ሰዎች 8 መድረሱን የኦሮሚያ መስተዳድር ገለጸ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

እንደአዲስ ባገረሸው የህዝባዊ እምቢተኝነትና ተቃውሞ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በንጹሃን ኢትዮጵያውያኖች ላይ ዳግም የመግደልና የማቁሰል ድርጊትን መፈጸማቸው ታውቋል።

የታሰሩት የፖለቲካ መሪዎች በአፋጣኝ እንዲፈቱ በመጠየቅ ለሰላማዊ ሰልፍ ወደ አደባባይ የወጡትን ሰልፈኞች የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በጥይት ለመበተን መሞከራቸው ተገልጿል።

በሻሸመኔ በተደረገው ህዝባዊ ተቃውሞ ከ30 በላይ የሚሆኑ ሰላማዊ ሰልፈኞች ጉዳት እንደደረሰባቸው እየተነገረ ሲገኝ የጉዳተኞቹ ቁጥር ከዚህ በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችልም ተጠቁሟል።

በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በተወሰደ እርምጃ ለሰላማዊ ሰልፍ በሻሸመኔ ከወጡት ሰልፈኞች መካከል መንግስት አራቱን መግደሉን ሲያምን የሟቾቹን ቁጥር መንግስት ሆን ብሎ ደብቋል እየተባለ ይገኛል።

በሃረርጌ የአገዛዙ የጸጥታ ሃይሎች በሰላማዊ ሰልፈኞቹ ላይ በከፈቱት ተኩስ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የሚወጡ መረጃዎች ሲያመለክቱ የተጎዱም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።

ይህን ህዝባዊ እምቢተኛነትና አገዛዙን የመቃወም ሰላማዊ ሰልፍን ተከትሎ መንግስት ከዚህ በፊት ያነሳውን የአስቸኩዋይ ጌዜ አዎጅ በድጋሜ ደንግጓል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለዚህ ሁሉ ጉዳትና ነፍስ መጥፋት አፍራሽ ኃይሎችን ተጠያቂ ሲያደርግ፣ አፍራሽ ኃይሎች ያላቸውን ግን በግልጽ አልጠቀሰም።

ሰልፈኞቹ በአጠቃላይ በህውሃት የሚመራው መንግስት ከስልጣን እንዲወርድ እንዲሁም በእስር እየተሰቃዩ የሚገኙትን የፓለቲካ አመራሮች በፍጥነት ነጻ እንዲወጡ ሲጠይቁ ተሰምተዋል።

መንግስትን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ከተጠራበት ከተሞች መካከል  አምቦ፣ ነቀምት፣ ጉዱሩ፣ ጊንጪ፣ ቡራዩና ሆሎታ፣ ሻሸመኔ፣ አዳባ፣ ባሌና ሐረርጌ ይገኙበታል።