እስራኤል የዩናይትድ ስቴትስን ውሳኔ በመከተል ከዩኔስኮ አባልነት እንደምትወጣ አሳወቀች

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

የፍልስጤምን አስተዳደር በዩኔስኮ (UNESCO) አባልነት የማቀፍ ውሳኔ ከተደረሰበት ከስድስት አመት ገደማ በፊት የጀመረው የዩናይትድ ስቴትስና የዩኔስኮ (UNESCO) የሻከረው ግንኙነት ዛሬ በዩናይትድ ስቴትስ ከሙሉ አባልነት  የመውጣት እርምጃ ተቋጭቷል።

የዩኔስኮ (UNESCO) የበላይ ሃላፊ የሆኑት አይሪን ቦኮቫ የዩናይትድ ስቴትስ ውሳኔ እንዳሳዘናቸውና ለዩኔስኮ ማህበረሰብ ትልቅ እጦት እንደሆነም ገልጸዋል። 

ፍልስጤም የዩኔስኮ ሙሉ አባል በመሆኗ ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ ለተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (UNESCO) የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ እኤአ በ2011 በከፍተኛ መጠን መቀነሷ ይታወቃል።

ይህን የአሜሪካንን ውሳኔ በመደገፍ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር አገራቸውም ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ የዩኔስኮ አባልነቷን እንደምትሰርዝ አስታውቀዋል። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ የዩናይትድ ስቴትስን ውሳኔ የጀግንነትና የሞራል ምሳሌ በማለት አሞካሽተውታል። 

የዩናይትድ ስቴትስን ከዩኔስኮ መውጣትን በመመርኮዝ የውጭ ጉዳይ ሚንስትራቸው በአፋጣኝ አገራቸው ሙሉ አባልነቷን እንደሰረዘች የሚያሳውቅ ደብዳቤ ለዩኔስኮ እንዲያዘጋጅና እንዲያቀርብ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ማዘዛቸውም ታውቋል። ከዩኔስኮ አባልነቷ እራሷን ብታወጣም በገለልተኛና በተመልካችነት የሚሳተፍ ቡድን ግን እንደምትመድብ ዩናይትድ ስቴትስ ገልጻለች።

የዩናይትድ ስቴትስ ከዩኔስኮ አባልነት ሙሉ በሙሉ የመውጣት ውሳኔ ተግባራዊ የሚሆነው በዲሴምበር እኤአ 2018 አከባቢ እንደሆነም ተዘግቧል።

እኤአ በ1945 በ37 አገራት አባልነት የተመሰረተው ዩኔስኮ (UNESCO) የአለማችንን ድንቅ ቅርጽንና ባህልን ከመጠበቅና ከማስተዋወቅ ያለፈ በትምህርት፣ በሳይንስ እንዲሁም በሰላምና መረጋጋት ዙሪያ የሚሰራ አለም አቀፋዊ ድርጅት ነው።