እውነትን ማወቅና ለእውነት መጋፈጥ ይለያያል (ኤልያስ ገብሩ)

ወጣቱ ፖለቲከኛ ሀብታሙ አያሌው ይህን ‹ከህወሓት ሰማይሥር› የተሰኘውን ሁለተኛ መጽሐፉን ለንባብ አብቅቷል፡፡ መጽሐፉ የሀብታሙን የሕይወት ውጣ ውረድ፣ የፖለቲካ ሕይወት ጅማሮ፣ ስሜቱን ስለተኮሰው የቅንጅት መንፈስ፣ በምን አጋጣሚና መንገድ ኢህአዴግ ቤት እንደተገኘ፣ በዚያም ስለነበረው ሚናና በቆይታው ምን እንዳስተዋለ፣ ከኢህአዴግ ካምፕ እንዴት እንደ ወጣ፣ በሒደትም የተቃውሞውን ጎራ በምን መልኩ እንደተቀላቀለ፣ በአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ውስጥም ስላደረገው አበርክቶ፣… በቅደም ተከተል ተርኮልናል፡፡

ይህ የሀብታሙ መጽሐፍ በበርካታ አስቀያሚ መጠላለፍ፣ በሴራ ወጥመድ፣ በፍረጃ አባዜ፣… ክፉኛ የተተበተበውና ያልዘመነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ጸሐፊው በሰኔ 2006 ዓ/ም በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ከታሰረ በኋላ ከጀመረው ሕመም ጋር በመታገል ዛሬም ድረስ ተገቢውን ሕክምና እንዳያገኝ በአገዛዙ በቂም በቀል ተከልክሎ እየተሰቃየ ያሰናዳው መጽሐፍ በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል፡፡

የሀብታሙን ጽናት ከአንዱ ጥግ ወደ ሌላኛው የሚያላጋቸውን ወጀብ ተቋቁመው የተፈጥሮ ጸዳል ያለማቋረጥ ከሚያንጸባርቁ አረንጓዴ የባሕር ዳር ሰንበሌጦች ጋር አመሳስለዋለሁ፡፡ በርካታ ሰዎች ወቅታዊ መሰናክሎችን ለመቋቋም ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ ሀብታሙ ግን የተራዘመ መከራን በትእግስት፣ በጽናትና በድፍረት በመወጣት ለብዙዎች የጥንካሬና የብርታት ተምሳሌት መሆን ችሏል፡፡

እውነት መራራ ናት ብዙ ዋጋ ታስከፍላለች፡፡ እውነትን ማወቅና ለእውነት መጋፈጥ ይለያያል፡፡ ብዙዎች እውነትን ያውቃሉ ነገር ግን በድፍረት ለመጋፈጥ በፍርሃት ይሸበባሉ፡፡ ጥቂቶች ግንእውነትን አውቀው መራራ ጽዋን ለመጎንጨት ይደፍራሉ፡፡

ከእነዚህ ጥቂቶች ውስጥ አንዱ ሀብታሙ አያሌው መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ሀብታሙ እውነቱን ተረድቶ እውነትን ፊት ለፊት በድፍረት የተጋፈጠና በዚህ ረገደ ሌሎችንም ማስከተል የቻለ ወጣት ፖለቲከኛ ነው፤ ይህም ዋጋ አስከፍሎታል፡፡ በአጠቃላይ ሀብታሙ አያሌው ለዛሬው ትውልድ አንዱ የጽናት፣ የብርታት፣ የጤናማ እልኸኝነትና ለእውነት ተጋፋጭነት ተምሳሌት መሆኑን አምናለሁ፡፡

            ኤልያስ ገብሩ

ለውጥ አቀንቃኝ ጋዜጠኛና ጦማሪ