እውነትን መታገል እንጂ ማሸነፍ አይቻልም (በየሸዋስ አሰፋ)

‹ከህወሓት ሰማይ ሥር› በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን የሀብታሙ አያሌውን መጽሐፍ ረቂቅ አንብቤ እንደጨረስኩ አካሉ ከርዕሱ ይገዝፋል አልኩ፡፡ ምክንያቱም ከልጅነት እስከ ወጣትነት፣ ከቤተክህነት እስከ ቤተ መንግሥት፣ ከቅንጅት እስከ አንድነት፣ ከገዢው ፓርቲ እስከ ወጣቶች ፎረምና እስከ ከተቃዋሚው አንድነት የሕዝብ ግንኙነት፣ ከአዲስ አበባ እስከ ኬፕታውን፤ እንዲሁም ከማዕከላዊ እስከ ቂሊንጦ የተረካቸው ሁነቶች በጠባቡ የህወሓት ሰማይ ሥር የሚሸከፉ ስላልመሰለኝ ነው፡፡

የሀብታሙ የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ላይ ያጋጠሙት ‹አማሳኝ› ካህን ለወገንና ለአገር ያለውን ተቆርቆሪነት ከውስጡ ፈንቅለው ያወጡ ብቻ ሳይሆኑ በቀኝና በግራ ደረት ኪሳቸው በያዙአቸው ሁለት የተለያዩ ‹ዓለማዊና መንፈሳዊ› መሣሪያዎቻቸው የቤተ ክህነቱና የቤተ መንግሥቱ ሴራ መጨባበጫ መሆናቸውን ፍንትው አድርጎ አሳይቶአል፡፡ እኚህ ሰው የጳውሎስና የመለስ ነጠላዎች የተሳሰሩባቸው በመሆናቸው ቀላል ሰው እንዳልነበሩ መገመት ይቻላል፡፡ ሀብታሙና ጓደኞቹ ይህንን ቋጠሮ ለመፍታት የሄዱበት መንገድና የገቡበት በር ሀብታሙ በመጽሐፉ በሚገባ ያስነብበናል፡፡

መንታዎቹ የአርከበና የመለስ መንገዶች በሚለው ርዕስ ሥር የህወሓቶች ፊት አውራሪዎች የመቆጣጠር አባዜ ለፎረሞቹ እንኳን ትንሽ መንከላወሻ ነጻነት እንደማይሰጡ ይገልፅልናል፡፡ የሴቶችና የወጣት ፎረሞች ለመቆጣጠር በሁለቱም ሰዎች የቀረቡትን አማራጮች ሲታዩ የበሽታቸውን ተመሳሳይነት ትረዳላችሁ፡፡ ለዚህም የሲቪል ማኅበራት ተብለው መሪዎች የኢህአዴግ አባል የሚሆኑበትን የመለስን ተንኮል ሀብታሙ ከውስጥ ወደውጭ ያሳየናል፡፡ እዚህ ላይ የህወሓት መሪዎች የፎረሞቹ አመራሮች እንዲያፈነግጡ የሚይዙበት ገመድ ኅብረተሰቡ ‹ወያኔ ናቸው› እንዲል በማድረግ መሆኑን ስናይ ለሰሚው ግራ ይሆንብናል፡፡ ለሕዝቡ ወያኔ የድርጅት ስም አይደለም፤ ስድብ እንጂ፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች ‹ውሻ› የእንስሳስም ሳይሆን ስድብ እንደ ሆነ ሁሉ እነመለስም ያንኑ እንዴት ፓለቲከ እንደሚሠሩበት ሀብታሙ በመጽሐፉ ከትቦልናል፡፡ ሌላም ሌላም … ሀብታሙን በደንብ የማውቀው እስር ቤት ውስጥ ነው፡፡ ከመጽሐፉ ውስጥ እሱን ይገልፃል ብዬ በተለየ የማስበው ስለ ፓርቲው ምስቅልቅል በገለፀበት ሥር በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ በሚል ርዕስ የጻፈው ነው፡፡ በአንድ በኩል የወያኔ ልዑክ በሌላ በኩል የግንቦት ሰባት ልዑክ የሚሉ የምላስ ጦሮች ሲወጉት አይቻለሁ፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ያለው ይዘት ይሄ ባይሆንም እኔ ግን ሀብታሙን በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ያደረጉት እነዚህ ሞረዶች ይመስሉኛል ፡፡ ሀብታሙ በእድሜ ልጅ ነው በአስተሳሰብ ያበሰለው ይኸው በሁለት በኩል መጠበሱ ጭምር ይመስለኛል፡፡

ህወሓት ቢጠብሰው ብዙ ላይደንቀኝ ይችላል በተቃውሞ በኩል ያለው ግን ከማብሰል አልፎ ያሳረረው ይመስለኛል፡፡ እሱስ ቢሆን በበላይ ዘለቀ አንገት ላይ ገመድ ካጠለቀች ጉደኛ አገር ምን ይጠበቃል፡፡

የሆነው ሆኖ የሀብታሙን መጽሐፍ ረቂቅ የገለፅኩት ሀብታሙ ማዕከላዊን የገለፀበትን ታክል በጨረፍታ ነው፡፡ በውስጡ ከግል  ሕይወት እስከ ፓርቲ ተሳትፎ ከመንግሥት ሥልጣን እስከ አገራዊ ኃላፊነት ከእስር ቤት እስከ አሻንጉሊቱ ፍርድ ቤት የተዘረዘሩ በርካታ ቁምነገሮችን እያነሣ የሕይወት ምንጭ ከሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እያጣቀሰ ብዙ እውነቶችን ይዞልን ቀርቦአል፡፡