በቄሮ ስም ንብረት የሚያወድሙ የህወሃት ሰላዮች ተያዙ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

እየተካሄደ ባለው ኦሮሚያ አቀፍ ህዝባዊ እምቢተኝነትና ትእይንተ ህዝብ በአንዳንድ ከተሞች ከሰላማዊ ሰልፈኛው ፍላጎትና መንፈስ ውጪ ቄሮ በመምሰል በንብረትና በህይወት ላይ አደጋ ሲያደርሱ የነበሩ ስውር የህወሃት የድህንነት አባሎችና ተቀጣሪዎች በኦሮሚያ ፖሊስ ሃይል ክትትልና በህዝቢ ጥረት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታወቀ።

ላለፉት ሁለት ቀናት በሰሜን ሸዋ አካባቢ በጫንጮና በገብረጉራቻ ንብረትነታቸው የአማራ ተወላጆች በሆኑት ላይ አደጋ በመጣል ከፍተኛ ውድመት ያደረሱትን በትውልድ ኦሮሞና የቄሮ አባል ያልሆኑ የትግራይና የደቡብ ክልል ተወላጆችን የኦሮሚያ ፖሊስ ሃይል በቁጥጥር ስር ማዋሉን ይፋ አድርጓል።

ከሳምንት በፊት በሻሸመኔና በቦኬ ከተሞች በተክሰተና የስድስት ሰዎች ህይወት በጠፋበት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ቄሮን ተመስለው የኦነግን ባንዲራ በመያዝና በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ለመከላከያ ሰራዊቱ በሰልፈኛው ላይ እንዲተኩስ ምክንያት የሆኑ አንድ የትግራይ ተወላንጅን ጨምሮ የደቡብ ተወላጅ የሆኑትን መቆጣጠሩን የኦሮሚያ ፖሊስ ይፋ አድርጓል።

በኦሮሚያ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ እምቢተኝነትና ሰላማዊ ተቃውሞ ስርዓቱ ረብሻና ብጥጥብጥ ፈጥረዋል እያለ የሃይል እርምጃ ለመውሰድ እራሱ ያሰለጠናቸውን ልዩ ሃይሎችን አመሳስሎ በማሰማራት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም በአብዛኞቹ ከተሞች በህዝቡ በቄሮዎቹ እና በኦሮሚያ ፖሊስ ሃይል ንቁ እርምጃ እንዲከሽፍ የተደረገ ሲሆን ውስን በሆኑ ስፍራዎች እንደ ሻሸመኔ፣ ጫንጮ እና ገብረጉራቻ ባሉ ከተሞች ከህዝባዊው እምቢተኛና ሰላማዊ ሰልፈኛ ህዝብ ፍላጎትና ዓላማ ውጪ ሆን ተብሎ የህዝቡን ፍትሃዊና ሰላማዊ ጥያቄን ለማጠልሸት ንብረት የማውደም ተግባራት የተፈጸሙ ቢሆንም የአድራጊዎቹ ማንነትና ዓላማ ከህወሃት በኩል መሆኑን የኦሮሚያ ፖሊስ ሃይል ማጋለጡኝ መረዳት ተችሏል።

በመሳሪያ አፈሙዝ ወደ ስልጣን የመጣውና ሀገሪቷን በቋንቋ ሸንሽኖ በግድ እየገዛ ያለው ህወሃት መራሹ ስርዓት በስልጣን ላይ ለመቆየት በነገዶች መካከል ከፍተኛ ፍጅትና እልቂት በመፍጠርና ብሎም በአማራና ኦሮሞ መካከል ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲነሳ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያሉትን የአማራ ተወላጆች ንብረትና ህልውና በስውር ባሰማራቸው ሰላዮቹ በቄሮዎች ስም ሲፈጽምና ሲያስፈጽም እንዳለ በይፋ እየተጋለጠ መሆኑን እያየን ነው።

በተለያየ የመገናኛ ብዙሃን በርካታ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች የህወሃት ስርዓት ባዘጋጃቸው ግርፎቹ ሆን ብሎ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ተግባራትን እየፈጸመ ነው የሚል ጥቆማ በተደጋጋሚ ግዜ ሲገልጹ የነበረ ሲሆን ዛሬ ግን ድርጊቱ በኦሮሚያ ፖሊስ በኩል በይፋ የታየ ማስረጃ መያዙ የስርዓቱን ጸረ ሰላምነትና ጸረ ህዝብነት በይፋ ያረጋግጣል ሲሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ።