ዶ/ር ቴድሮስ የሮበርት ሙጋቤን ሹመት ለመሰረዝ ተገደዱ

0

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የድርጅቱ በጎ ፍቃድ አምባሳደር አድርገው የሾሟቸውን ፕሬዚዳንት ሮበረት ሙጋቤን ሹመት ለመሰረዝ መገደዳቸውን ዛሬ ማምሻውን አልጀዚራ ዘገበ።

ዶ/ር ቴድሮስ የፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን የድርጅቱ በጎ ፈቃድ አምባሳደር አድርገው መሾማቸውን ካስታወቁ ሰዓታት በኋላ ከብዙ አቅጣጫ የተሰነዘረባቸውን ብርቱ ትችትና ነቀፌታን በመከላከልና ብሎም የሾሟቸውን ሰው ብቃት በማስረዳት መሞገት የጀመሩ ቢሆንም ከአሜሪካ፣ አውሮፓና ከሚመሩት ድርጅት ነቀፌታው ጠንክሮ በመቀጠሉ የሰጡትን ሹመት ለማንሳት እንደተገደዱ ነው መረዳት የተቻለው።

የአየርላንድ ምኒስትር ሙጋቤ የWHO መሰረታዊ ዓላማን በመተግበር ደረጃ አንዳችም ያስመዘገቡት ውጤት ሳይኖር ዛሬ የድርጅቱ በጎ ፈቃድ አምባሳደር ተደርገው በድርጅቱ ዳይሬክተር መሾም እጅግ የሚገርምና ትርጉም አልባ ሆኖ ነው የሚታየኝ ያሉ ሲሆን የድርጅቱ [WHO] ወሳኝ የሆኑ ሃላፊዎችም የዶ/ሩን ተግባር በትዊተር ገጾቻቸው ላይ ክፉኛ ሲያብጠለጥሏቸው ታይተዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከድርጅቱ ውስጥና ውጭ የተከፈተባቸውን ፈታኝ ትችት፣ ነቀፌታና ተቃውሞ መቋቋም አቅቷቸው ለሚመሩት ድርጅት [WHO] በጎ ፈቃድ አምባሳደር አድርገው የሾሟቸውን የዚምባቡዌን ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን በ72 ሰዓታት ባነሰ ግዜ ውስጥ ውሳኔያቸውን ሽረው ሹመቱን ለመሰረዝ መገደዳቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ሮበርት ሙጋቤ የመሾም ተግባር አሜሪካ አሳዛኝ ያለችው ሲሆን ከሃያ የሚበልጡ በጤና ነክ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ውሳኔውን አውግዘው ደብዳቤ የጻፉ መሆናቸውም የተገለጸ ሲሆን ዶ/ሩን ክፉኛ እንዳስጨነቀ መረዳት ተችሏል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃና የውጭ ጉዳይ ምኒስትር የነበሩት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ባለፈው ግንቦት ለድርጅቱ [WHO] ዋና ዳይሬክተርነት በሚወዳደሩበት ወቅት በርካታ ኢትዮጵያውያን የሰውዬውን የሀገር ቤት ሪኮርድ በመጥቀስ ክፉኛ ሲቃወሟቸው እንደነበረ አይዘነጋም።