ምስል ከፋይል

የዐለማችንን ምርጥ ጦረኛ የነበረውን አይበገሬውን ታላቁን አሌክሳንደር ያፈራች አገር ነች። ከመከረኞች ጋር ዕድሜ ልኳን ከምትችለው በላይ የራስዋ ያልሆነውን መከራ ስትሸከም የኖረችው የፃድቋ እናት ቴሬዛ የትውልድ ሥፍራ ነች። እንደኛ እናት ኢትዮጵያ ረጅምና ውስብስብ ታሪክ ያላት አገር ነች። መጠሪያ ሥምዋ ችግር ስለፈጠረባት ቸኩዬ ከመጥራት ልቆጠብና ስለአንዳንድ እውነታ መጫወታችንን እንቀጥል።  ኢትዮጵያን ካነሳን ሌላም የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። የኢትዮጵያ መሪዎች ስላልፈለጉትና ግመሎቹ እንዲጠጡበት ብለው ነው። የስዋ መሪዎች ግን ሁኔታው አልፈቅድ ብሎ እንጂ ለተጠማ ግመል ብለው የአባቶቻቸውን አደራ አሽቀንጥረው የሚጥሉ ባለጌዎች አይደሉም። ሁለቱም የባህር በር የላቸውም። የቀድሞ እህቶችዋ ቦምብ እንደዝናብ ሌት ተቀን ለረዥም ጊዜ ያለማቁዋረጥ ወርዶባቸው ያገኙትን፥ ይህች አገር ግን ቅጠል ኮሽ ሳይልባት ነው በሰላም፥ በሕዝባዊ ድምፅ ብቻ ጎጆ የወጣቺው። በሰሜን ምዕራብ ኮሶቮ፥ በሰሜን ሰርቢያ፥ በምሥራቅ ቡልጋሪያ፥ በደቡብ ግሪክ፥ በምእራብ ደግሞ አልባኒያ ያዋስኑዋታል። በተራሮች ብዛትና የከፍታ ነጥቦች ተወዳዳሪ አገር አይገኝላትም። በተፈጥሮ መስህብና ታሪካዊ ቦታዎች እጅግ የታደለች ነች። በኦፕየም ምርትዋ ጥራት ተጠቃሽ ናት። የስዋ ኦፕየም 14 ሞርፊን ሲኖረው የቻይና 8 ብቻ ነው ያለው። የሕዝብ ብዛትዋ ከሁለት ሚሊዮን ጥቂት ነው የሚዘለው። 62 በመቶው ሕዝብ በአገሪቱ መጠሪያ ቃል የሚጠራውን ቁዋንቁዋ ተናጋሪ ሲሆን 25 በመቶው ደግሞ የአልባኒያ ዝርያ አላቸው። የቱርክና የሮማኒ ዝርያ ያላቸው 4 ና 2 በመቶ ናቸው። ሃያ አምሥት ሺ ኪሎሜትር ስኩዌር የቆዳ ሥፋት አላት።

በ1991 በተደረገ ሕዝበ ውሳኔ ራሥዋን የቻለችው አገር በ2004 ለአውሮፓ ማኅበር አባልነት ያቀረበችው ጥያቄ እስካሁን ተቀባይነት አላገኘም። ምክንያቱ ደግሞ ከግሪክ የተነሳው ከፈለግሽ ሥምሽን ቀይሪ እንጂ ይህን ሥም ይዘሽ ማኅበሩን አትቀላቀዪም ተቃውሞ ነው። ቀልድ ሊመስል ይችላል። በአገራችን ያሉ ቃልቻዎች ታመው አልድን ያሉ ልጆችን ሥም ማስቀየርን እንደመፍትሄ እንደሚያቀርቡት ሁሉ። ታዲያ የታመመችው ይህች ታሪኩዋን የምናወሳላት አገር አይደለችም። ግሪክ በሽታው ሊመጣባት እንደሚችል ቃልቻ ሳይሆን መልዓክ ሹክ ያላት ነው የሚመስለው። እርምጃው አገሩን የሚወድ ማንም መሪ ሊወስደው የሚገባ እርምጃ ነው። ወደ ግሪክ ታሪክ ተመልሠን እንመጣለን። አገር ካልተበታተነና የሕዝብ ደም ካልፈሠሠ እንደውሻ የሚያክለፈልፈው የህወሀት መንግሥትን እርምጃና የዖጋዴን ግዛት ሁኔታ እንመልከት።

ዖጋዴን ህወሀት ሥልጣን ላይ እስከተፈናጠጠበት ወቅት ድረስ የአብዛኛውን የሃረርጌና የባሌ ክፍለሐገሮችን ክፍል የሚሸፍንና ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ የሶማልኛ ቁዋንቁዋ ተናጋሪና በእሥልምና ሃይማኖት ተከታይ ሕዝብ የተሞላ ክፍል ነው። የቆዳ ሥፋቱ 240,000 ሥኩዌር ኪሎ ሜትር ይሽፍናል። 142 ሚሊዮን ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ጋስ ዕምቅ ሀብት በዚሁ ግዛት ውስጥ እንደሚገኝ ይገመታል። የቤት እንስሳ ሀብቱ የደለበ ነው። አብዛኛው ሕዝብ በከብት እርባታ የሚተዳደር ሲሆን በእጣን ምርቱም ይታወቃል። በምሥራቅ አቅጣጫ ኢትዮጵያን ከጅቡቲ፥ ከሶማሊያና ከኬንያ ያዋስናታል። በ13ኛውና 14ኛው ክፍለ ዘመናት አካባቢውን ይመሩት የነበሩ የኢፋት ሡልጣኖች እስከ ሸዋ ድረስ ዘልቀው የሚቆጣጠሩበት ወቅትም ነበር። ተደጋጋሚ ግጭቶች አካባቢውን በሚያስተዳድሩት ሡልጣኖችና የሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል በሚያስተዳድሩት ክርስቲያኖች መካከል ይደረጉ ነበር። በ16ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በግራኝ አህመድ ወረራ አብዛኛውን የሠሜን ኢትዮጵያን ክፍል መቆጣጠር ችለውም ነበር። በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ዐፄ ሚኒሊክ የሚመሩት ጦር ግዛቱን ተቆጣጥሮታል። በ1936 ጣሊያኖች ከኢጣሊያ ሶማሊላንድ ጋር አጣምረው ገዝተውትም ነበር። የኢጣልያን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሽንፈት ተከትሎ እንግሊዞች ከብሪቲሽ ሶማሌላንድ ጋር አጣምረው ለመግዛት በነበራቸው እቅድ የታላቋ ሶማሊያን በሽታ ከተከሉ በሁዋላ ግዛቱን ለኢትዮጵያ በ1954 መልሰውታል። የኃይለሥላሤና የደርግ መንግሥታት ከነፃ አውጪ ቡድንና ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ግዛቱን የራሣቸው ለማድረግ በጦርነት ሲፋለሙ ቆይተው የኢትዮጵያን አንድነት እንዳሥጠበቁ አልፈዋል። ህወሀት በአሁኑ ወቅት ይህ ዖጋዴን ይባል የነበረውን አካባቢ 40,000 ሥኩዌር ኪሎሜትር አክሎበት የሶማሌ ክልል በማለት ሰይሞታል።

እስቲ ወደግሪክ እንመለስና ከመጠሪያ ዘሎ ምንም ተፅዕኖ የለውም ተብሎ የሚታሰበው የሥም ጉዳይ ለምንድን ነው ያስጨነቃትና እንደዚህ መንቻካ ያደረጋት? ብለን እንጠይቅ። ግሪክ 11 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት በአፍሪካ፥ በአውሮፓና በእስያ መገናኛ ስትራቴጂካዊ የሆነ ቦታ ወደ 130,000 ኪሎሜትር ስኩዌር ላይ የሠፈረች እጅግ ጥንታዊነት ያላት አገር ናት። ለምዕራቡ ዓለም ሥልጣኔና ፍልሥፍና መነሻ፥ ዲሞክራሲን፥ የዖሎምፒክ ጨዋታዎችን፥ የምዕራቡን ዓለም ሥነፅሁፍን፥ ታሪክን፥ ፖሎቲካ ሣይንሥን፥ ሣይንሥና ሒሳብን እንዲሁም የምዕራቡን ዓለም ድራማ የፈጠረች ታላቅ አገር ነች። ግሪክ የደሤት ግዛቶችዋን ሳይጨምር ዘጠኝ የመሥተዳድር ክልሎች አሉዋት። ከነዚህም ትልቁ መቄዶንያ ተብሎ ይጠራል። 2.4 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት የግሪክ አካል የሆነችው የሜቆዶንያ ክልል ሕዝብዋ ግሪክኛ መናገር ባያቅተውም የሕዝቡ በዕለት ተዕለት ኑሮውና የትምህርት ቁዋንቁዋው መቄዶንኛ ነው።

ከላይ በመግቢያችን ላይ ያስተዋወቅናት የቀድሞ ዩጎዝላቪያ ሥባሪ፥ ገና ጎጆ በወጣችበት ሠዓት ነው ከአሁን በሁዋላ “የመቄዶንያ ሪፑብሊክ” ብላችሁ ጥሩኝ ብላ ለዓለም ማመልከቻዋን ያስገባችው። ግሪክ አንገቴ ይቆረጥ ይህ ሥም ካልተቀየረ አለች። በነገሩ ግራ የተጋቡት ዓለም ዓቀፍ ተቁዋማት ዓለም ዓቀፍ ጉባዔ አካሂደው ዳቦ ሲቆርሡ ባይታዩም ማስታረቂያ ያሉትን “ሜቄዶንያ የቀድሞ ዩጎዝላቪያ ሪፑብሊክ” የሚል ሥም አወጡ። ይህ ሥም በተባበሩት መንግሥታት ፀሐፊ በኩል በጥር 22 1993 በዓለም እንዲናኝ ተደረገ። በሦሥተኛው ቀን የግሪኩ ውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር ሚካዔል ፓፓኮስታኒኖ ለተባበሩት መንግሥታት በፃፉት ደብዳቤ መቄዶኒያ የሚለው ቃል በጭራሽ ከስያሜው ውስጥ ድራሹ ካልጠፋ በአካባቢው የሠላም መደፍረሥን የሚያስከትልና አደገኛ መሆኑንም በመግለፅ ተቃወሙት። የሥም ፈላጊዋ አዲሢቱ አገር ፕሬዚደንት ኪሎ ግሪጎሮቭ ተቃውሞዋቸውን ያደረጉት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቀድመው በጥር 24 ነበር። ደብዳቤያቸው ዩጎዝላቪያ የሚለው ቃል በምንም መልኩ ከአገራቸው ሥም ጋር ተያይዞ እንዳይጠቀስ የሚከለክል ነበር። ምክንያቱንም ሲገልፅ ሰርቢያ ነገ ልትውጠን ትችላለች አሁንም እየጎመዠችን ነው የሚል ዓይነት መልዕክት ነበረው። በሥም የተነሣው ውዝግብ ይኸው መቁዋጫ ሳያገኝ ሩብ ምዕተ ዓመት ሆነው። ግሪክ የመቄዶንያ ዝርያ ያላቸው የስዋ ግዛት ክፍል የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ ብለው ክደውኝ ይሄዳሉ የሚል ፍራቻ ያላት ሲሆን፤ አዲሢቱም አገር ሠርቢያ ትናንት አንድ ነበርን ነገም አንድ እንሁን ጭቅጭቅ እንዳትፈጥር በመሥጋት ነው። የሰው አገር ፖሎቲካን ማቡካት ትተን ወደ ራሣችን እንመለስ። እነሱ የሚያቦካላቸው ብቻ ሳይሆን ጋግሮ የሚያጎርሣቸውም ሞልቶዋቸዋል። በነዚህ ሁለት አገሮች ጉዳይ ከልዕለ ኃያል አገር ፕሬዝዳንት ከጆርጅ ቡሽ አንሥቶ እስከ የተባበሩት መንግሥታት ዘርፎች እጁን እየከተተ ለማቡካት ያልሞከረ የለም – የሥም ማውጫው ዳቦ አልተጋገረም እንጂ ፥ ሊጋገር ቀርቶ ኩፍም አላለ።

ይህ ፅሁፍ የባልካን አገሮችን ታሪክ ለማሰስ ያቀደ ሣይሆን ሌሎች አገሮች እንደዚህ ያዙኝ ልቀቁኝ እያሉ የሚናቆሩበትን የአገር ወይም የአገር ክፍልን ሥያሜ ህወሀት ያለምንም ችግር እያነሳ ሲለጥፍ ድንቁርና ነው ወይስ ከጀርባ የታሰበ ክፋት ኖሮ የሚለውን ጥያቄ አንስቶ ከቀናን መልስ ለማግኘት ነው።  በእርግጥ ሁለቱም የህወሃት ባሕርይ መሆናቸው አይካድም።

ሶማሌ ክልል ፐርፎሬሽን

ፐርፎረሽን የሚለውን ቃል የሚተካ የአማርኛ ቃል ለማግኘት ባለመቻሌ ለቅሽምናዬ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ክፍያ ልትፈፅሙ ቼካችሁ ላይ ከፈረማችሁ በሁዋላ ቼኩን ሳብ ሥታደርጉት በቀላሉ ከጥራዙ ይላቀቃል። ምክንያቱም በሚላቀቅበት ቦታ ላይ ቀድሞውኑ፥ ጥራዙ እናንተ እጅ ሳይገባ በፊት፥ ፐርፎሬትድ ተደርጎ ስለነበር ነው። ልክ እንደቼኩ ጥራዝ የኢትዮጵያ ክልሎች በሕወሃት የአገዛዝ ዘመን ሙሉ ፐርፎሬሽን ሲደረግባቸው ነው የኖሩት። የዖጋዴን ወይም የሶማሊያ ክልል ደግሞ የባሰ ነው።

ፐርፎሬሽን 1. የአካባቢውን ሥያሜ መቀየር

ከላይ እንደጠቀስነው ይህ የአገር ክፍል ዖጋዴን የሚለውን ሥያሜ አሽቀንጥሮ ጥሎ፥ የሶማሊ ክልል ተብሎ ተሠይሞዋል። መንግሥት የሚለው ቃልም ታክሎለታል። እንደ መንግሥት የመወሠን ሥልጣን ግን አልተፈቀደለትም። ይህ ክልል በምሥራቁ አቅጣጫ ከሶማሊያ ፌዴራል ሪፑብሊክ ጋር ይዋሰናል። የሶማሊያ ፌዴራል ሪፑብሊክ 85 በመቶ የሶማሌ ዝርያ ያላቸው ወደ 16 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ባለቤትና ከአፍሪካ አገሮች በሙሉ ረዥም የባህር ዳርቻ ያላት አገር ነች። ዚያድ ባሬ ጎሣዎችን አንዱን ተጣቃሚ ሌላውን ተጎጂ ያደርግ የነበረውን አሠራሩን ተከትሎ በጎሳዎች መቆራቆሥ ምክንያት ላለፉት ሦሥት አሥር ዓመታት መረጋጋትና ማዕከላዊ መንግሥት አልባ ሆና ቆይታለች። ህወሀት የምእራቡን ዓለም ጥቅም ለማስጥበቅና የራሡን የውስጥ ፖለቲካ ግለት ለማቀዝቀዝ ሲል ለሶማሊያ አለመረጋጋት የላቀ ድርሻ አበርክቶዋል። አለመረጋጋትዋ ይዞዋት ነው እንጂ ይህች አገር ይህ አሁን ህወሀት የሦማሌ ክልል ብሎ ከሰየመው ግዛት የሚበልጥ መሬት ከኢትዮጵያ ይገባኛል እያለች ተደጋጋሚ ጦርነት ስትከፍት የቆየችበትን አጀንዳ በይፋ አልቀለበሰችም። ቱርክ አሜሪካንን ጨምሮ ከምዕራቡ ኃያላን ጋር ኩርዲስታኖችን በተመለከተ ዱላ ቀረሽ ውዝግብ ውስጥ ስትገባ፥ ግሪክ ይህ ሥም እኔ ቆሜ አይፅድቅም ብላ ሽንጡዋን ይዛ ስትከራከር፤ መቄዶንያ በፈጠራችሁ ዩጎዝላቪያ የሚል ሥም በእኔ ሥም ውስጥ አትደንቅሩብኝ ስትል፤ ህወሀት ግን የሶማሌ ክልል ብሎ ከሶማሊያ ፌዴራል ሪፑብሊክ ጋር የሚዋሰነውን የአገራችንን ክፍል መሠየሙ የሚያሳየው ኢትዮጵያን ሁላችንም ከምንገምተው በላይ እንደሚጠላት ብቻ ነው።

ፐርፎሬሽን 2. በክልሉ እየተደረገ ያለው ቅጥ ያጣ ጭፍጨፋ

በዓሉ ግርማ በቀይ ኮኮብ ዘመቻ ሲደረግ የነበረው ወታደራዊ እርምጃ የታሰበው ግብ ላይ እንደማያደርስ ከሰው ቀድሞ ተረድቶት በፊያሜታ አንደበት ኣድርጎ መፍትሄ ጠቁሞ ነበር። ጥይትና ቦምብ ብቻውን ለውጥ አያመጣም። የሕዝቡን ፍላጎት ተረዱት ሲራብ ድረሡለት፥ ሲጠማ አጠጡት፥ ሲታረዝ አልብሱት፥ ሲታመም መድሐኒት አቅርቡለት ብሎ። ፍቅርና ወዳጅነትን አሣዩት ብሎም ነበር። ለነገሩ የሚሠማ የለም እንጂ ክርሥቶሥም ያለው ይህንኑ ነበር። ማወቅ አንዳንድ ጊዜ ዕዳ መግባት ነው፥ በሕይወት የምትከፍለው። ሁለቱም በማስተማራቸው ተሰዉ። አንዱ ለእናት ኢትዮጵያ ሌላው ለሰው ልጅ። የሰው ልጅ ዳነ። ኢትዮጵያ እያጣጣረች ነው። አቤት ስንትና ስንት የኢትዮጵያ ሠማዕታት ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ ቀርቶዋል። ይኸው አሁን በዓሉ የፈራው ደርሦ ኤርትራ ወዳጅ ጎረቤት እንኩዋን መሆን ሳትችል ጭራሽ ጠላት ተብላ ተፈርጃለች።

ህወሀት በዚህ የሶማሌ ክልል ብሎ በሠየመው የአገር ክፍል ላይ እየፈፀመ ያለው ግፍ ግን ምናልባትም ከማዕከላዊ እሥር ቤት ሌላ ተወዳዳሪ የለውም። የዜጎች የምድር ሢዖል የሆነው ማዕከላዊ በአገሪቱ መዲና እምብርት ይገኛል። በሩ ግን ለእሥረኞችና ሠቆቃ ፈፃሚዎች ካልሆነ ለሌላው ሰው በሙሉ ዝግ ነው። የሦማሌ ክልልም ዳር አገር ከመገኘቱ በቀር እንደ ማዕከላዊ ለሌላው ሰው ዕርዳታ አቅራቢዎችን ጨምሮ ዝግ ነው። ሪፖርት የሚደረጉት ሠቆቃዎች ሀብታሙ ጣዕረ ሞት በሸነቆረለት ቀዳዳ እንዳመለጠው ሁሉ ዕድል በሸነቆረላቸው ቀዳዳ ሾልከውና ከክልሉ አምልጠው በጎረቤት አገሮች ከሠብአዊ መብት ጥበቃ ድርጅቶች ጋር ከተገናኙ ምሥኪን ግፉዓን ነው።

የዖጋዴን ብሔራዊ የነፃነት ግንባር በሚያዝያ ወር 2007 በነዳጅ ፍለጋ ላይ ተሠማርቶ በነበረ የቻይና ኩባንያ ላይ አደጋ ጥሎ የኩባንያውን ሠራተኞች መግደል ተከትሎ፤ ህወሀት ያቁዋቁዋመው ልዩ ፖሊስ፥ ለጭካኔው አምሣያ የማይገኝለት፥ ተኩሦ ለመግደል በቂ ምክንያት የማያሥፈልገው፥ በግሩፕ አስገድዶ ለመድፈር ከሥሜቱ አለመነሣሣት በቀር ምንም ከልካይ የሌለው፥ የዘረፈውን የሲቪል ዜጎችን ንብረት እንደ ጦር ምርኮ እንዲጠቀምበት የተፈቀደለት፥ የህወሀት ዕድሜ እስካለ ድረሥ በምንም ዓይነት ወንጀል ላይጠየቅ ቃል የተገባለት፤ ጭካኔን፥ ብልግናንና ወታደራዊ ሥልጠና ከህወሀት ጄኔራሎች በቅጡ የወሰደና ዘመናዊ ትጥቅ ያነገተ የአውሬዎች ቡድን ነው። በተለያዩ ድረ ገፆች ላይ ተለቆ የነበረ የአስከሬን ድርድር ቪድዮ ብዙ ሰው ሳይመለከተው አልቀረም። “ወደእዚህ አምጣ በለው እዛጋኮ ወንድሙ አለ” ሲል ይደመጣል ተናጋሪው። እግዚአብሔር ያሳያችሁ አንዱን ሰለባ የወንድሙን አሥከሬን እያሸከሙት ነው፤ ታደሉ ተማምንን የልጅዋ አሥከሬን ላይ እንደአስቀመጡዋት ሁሉ። የትግራይ ሕዝብ እኮ ሥጋ አደይ ማርያምን! ጥልቅ ሃይማኖተኛ ነው። እነዚህ ማን ወልዶ ያሣደጋቸው ጉዶች እንደሆኑ አቡነ አረጋዊ ይወቁት።

ሁይማን ራይትስ ዎች በጁን 12, 2008 ካወጣው ረፖርት ግፉዓን የሠጡትን ምሥክርነት እሥቲ እንመልከት:

“ወታደሮች ላሄሎውን ካቃጠሉ በሁዋላ ወደ አሌን መጡ እናም አሌንን አቃጠሉ። እኛ በወቅቱ እዛ ነበርን። ሁሉም ሰው ከቤቱ እንዲወጣ አዘዙን በአንድ ቦታ እንድንሰባሰብ አደረጉ ከዛም አዛዣቸው መንደሩ እንዲቃጠል አዘዘ። አዛዡ ወደእኛ ዞሮ በትንንሽ መንደሮች መኖር እንድናቆም ነግሮን እንደነበር አስታወሰንና ከአካባቢው እንድንርቅ አስገደዱን። ቤቶቹ ሣር ቤቶች እንደመሆናቸው ገና ሲለኩሱዋቸው ተንበለበሉ። መንደሮቹም ወደሙ በቃ።”

ሰፕቴምበር 23, 2007 በአንድ የመንደሩ ነዋሪ

“በክላሺንኮቭ ሠደፍ ቀጠቀጡኝ። ጥርሤ ላይ መቱኝና ጥርሤ ተሠበረ። ጀርባዬንና እግሬን በጎማ እየጠበጠቡኝ ከአንድ ሠዓት በላይ ቆዩ። ከዛም ሁለት እግሮቼን በገመድ አስረው ዘቅዝቀው ሠቀሉኝና የቻሉትን ያህል እየገረፉኝ የእምነት ቃሌን እንድሠጥ ጠየቁኝ። ይህ ሁኔታ ለሁለት ወራት በየቀኑ ማታማታ ቀጠለ።”

ሰብቴምበር 20, 2007 አንድ ባለ ሡቅ

“ከሌሎች ሁለት ሰዎች ጋር ከሀሠን አብዲ አብዱላሂ ና አሕመድ ጋኒ አብዱላሂ ጋር ከነበርንበት ቦታ ይዘውን ሄዱ። መጀመሪያ ሢባጎ በሁለቱም ጉዋደኞቼ አንገት ላይ አዞሩና በተቃራኒ አቅጣጫ ጎተቱት። ሁለቱም ወደቁ። እነሱ ላይ ይህን ሲፈፅሙ እኔን ጉርጉዋድ ውስጥ ጥለውኝ ነበር። አንድ ወታደር ወደኔ መጥቶ ጠመንጃውን ለማፅዳት በሚጠቀምበት የብረት ዘንግ አንገቴ ላይ ወደታች በመግፋት ሊያንቀኝ ሞከረ። እኔም እስኪለቀኝ ድረስ ጣቱን ጠመዘዝኩት። ከዛም ሁለት ወታደሮች መጥተው ሲባጎ በአንገቴ ዙሪያ አድርገው በተቃራኒ አቅጣጫ መጎተት ጀመሩ። ራሤን ሳውቅ በጉድጉዋዱ ውስጥ ራቁቱን የሆነ አሥከሬን ከላዬ ተጭኖብኝ መፈናፈን አልችልም ነበር፤ ውሃ ልትቀዳ ወደቦታው የመጣች አንዲት ሴት ባትረዳኝ ኖሮ። አሥከሬኑ የአሕመድ ጋኒ አብዱላሂ ነበር።

ረድዋን ሀሰን ኦክቶበር 30, 2007

ይህን ሁሉ ግፍና ሠቆቃ የሚወርድበትን ሕዝብ የእኛ ዜጋና የኢትዮጵያ ልጅ ነህ ብሎ ለማሳመን እንዴት እንደሚከብድ ለማስረዳት የግድ የግፍ ዱላን መቅመስ የሚኖርብን አይመስላኝም።

ፐርፎሬሽን 3. ከክልሉ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ማስወጣት

ህወሀት ኢትዮጵያን ተቆጣጥሮ ምንም ያህል ጊዜ ሳይወስድ ነው በጠቅላይ ሚኒሥትር ደረጃ ያለ ባለሥልጣኑን ወደምሥራቁ የአገራችን ክፍል ልኮ ከበረሀ በመጣ በመደዴ አፋቸው “ትላንት ሽርጣም ሲሉህ የነበሩትን ዛሬ ጊዜህ ነውና አሳያቸው።” እያሉ የሰበኩት። ካድሬዎቻቸውና ጥቂት ጥቅመኞች ተታለው የተፈለገውን ጉዳት ቢያደርሱም አብሮ የኖረን ሕዝብ ማነሳሳቱ አልተሳካላቸውም ነበር። አማራና ጉራጌ ከአካባቢያችን ይውጣ የሚል ሠልፍ ጠዋት አቀናብረው ያለእፍርት ለምሣ ሠዓት የሬዲዮ ዜና አድርሠውት ነበር። የዜናው ቀፋፊነት ብቻ ሣይሆን የቀረበበትም የንባብ ቃና እጅግ ሠቅጣጭና ለረጅም ጊዜ ህሊናን የሚያሥጨንቅ ነበር። በዚህ ምክንያት የተፈናቀሉም አያሌ ነበሩ። ታዲያ የኔ አገር የት ነው ይሄስ አገር የማን ነው ብለው መልሥ ያላገኘ ጥያቄ የጠየቁ ብዙ ኢትዮጵያውያን ነበሩ።

ፐርፎሬሽን 4. የህወሀት ጦር ሶማሌን መውረር

ሶማሊያውያን በአሜሪካ ላይ በነበራቸው የመረረ ጥላቻ ለነፍሳቸው ሳይሳሱ ነበር ጦሩን የገጠሙትና ያለርኅራኄ በየጎዳናው ላይ አሥከሬናቸውን የጎተቱት። ጦርነቱ በብዙ የእሥልምና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በክርስቲያኒቱ አሜሪካና በተቀረው እሥላማዊው ዓለም መካከል የሚደረግ ጦርነት ተደርጎ ነበር የተወሰደው። የአሜሪካውያንን ሐገሪቱን ጥሎ መውጣት ተከትሎ የእሥልምና ፍርድ ቤቶች ኅብረት ባደረገው ከፍተኛ እንቅሥቃሤ አገሪቱን በማረጋጋት ረገድ ጥሩ ጅማሮ እያደረገ ነበር። ምርጫ 97ን ተከትሎ ወያኔ ከገባበት አጣብቂኝ አሜሪካ እንድታወጣው በልዋጩ ሕወሃት ኅብረቱን ሊወጋ የኢትዮጵያን ጦር አዘመተ። ኢትዮጵያ ገሚሡ ሕዝብዋ የእሥልምና ኃይማኖት ተከታይ መሆኑ፥ ከአምሥት ሚሊዮን በላይ በዘር በኃይማኖት በቁዋንቁዋ ከሚዘመትባት አገር ሕዝብ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ህዝብ ያላት አገር መሆንዋ ለወያኔ ቁብም አልሠጠውም። ሶማሊያ ረዥም የባህር በር ባለቤት ኢትዮጵያ ደግሞ የባሕር በር አልባ ሆነው በጉርብትና ነገን አብረው የሚኖሩ እንጂ እንደ አሜሪካኖቹ ጉዋዝዋን ጠቅልላ ከአካባቢው ልትሰወር እንደማትችል ህወሃትን ውልም አላለው። ወያኔ በዚህ ድርጊቱ በችግራቸው ወቅት መጠለያ በመስጠት ከኮሎኒያሊስቶቹ ዘመን ጀምሮ የተተከለውን የጠላትነት ሥሜት በማሻር ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥረት ውኃ ከለሰበት። በዚህ ንዴት የሱማሊያ ወጣቶች እየጎረፉ ገብተውለት አልሸባብን ከምንምነት ወደ አይበገሬ የአፍሪቃ ቀንድ ኃይል ቀየሩት። ይኸው ከአሥር ዓመት በላይ ጦርነቱ ተራዝሞ የኢትዮጵያ ወጣቶችን እየቀረጠፈ ይገኛል። ለወደፊቱም ቢሆን ምን አድርገን ይቅርታቸውን እንደምናገኝ አላህ ነው የሚያቀው። ኢትዮጵያ የራሥዋን የማትሰጥ የሰው የማትነካ ትርክታችን ግን የአሜሪካንን ጦርነት ለመዋጋት ስንል ሶማሊያን ነክተናልና፥ ለሱዳን መሬት ሠጥተናልና ለዘላለሙ ገደል ገብቶዋል።

ፐርፎሬሽን 5. የበጀት ዘረፋ

ህወሀት ከጨካኝነቱና ከከፋፋይነቱን ቀጥሎ ዘራፊነት ልዩ ባህሪው ነው። ገንዘብ የሚያስገኝ ከሆነ ምንም ያህል ነፍሥ ቢቀጠፍ ጉዳዩ አይደለም። የክልሎችን ፖሎቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ስልጣኖችን ሙሉ በሙሉ ነው የሚቆጣጠረው። ምንም የአሥተዳደር ነፃነት ለአካባቢው ተወላጆች የተሠጠ የለም። ሥራዎችን ሁሉ አንቆ ሣያሠራ እሥከ ዓመቱ መጨረሻ ይቆይና የክልሎችን በጀት፥ አልተጠቀሙበትም በሚል ምክንያት፥ በወዳጅነት ለፈረጀው ክልል እንዲዛወር ያደርጋል። ከገንዘቡ መዘረፍ የበለጠ የሚያንገበግበው ለበጀቱ ሥራ ላይ አለመዋል የሚቀርበው ምክንያት ነው። ይህም የአንድ አካባቢ ተወላጆች ኃላፊነት የጎደላቸው፥ በሱስ የተጠመዱ፥ ዕውቀት አልባዎች ሢሆኑ በአንፃሩ ደግሞ ያሉት የተማሩና የተመራመሩ፥ ኃላፊነት የሚሰማቸው ናቸው። በሁለት የተለያዩ የአንድ አገር ክፍሎች ውስጥ ከቁዋንቁዋ ልዩነት ባሻገር ይህን ያህል የክህሎት ልዩነት እያለ እንደ እንድ አገር መቀጠሉ ቶሎ መላ ካልተበጀለት አጠያያቂ ነው የሚሆነው። በተለይ ደግሞ ልዩነቱ የተፈጠረው ሕወሀት ላለፉት 25 ዓመታት የተከተለው የፖለቲካና የትምህርት ፖሊሲ አንዱን ክፍል በድሎ ለሌላው እያዳላ መሆኑ ሲታሰብ።

ፐርፎሬሽን 6. የመቶ ዓመት ታሪክ ፕሮፖጋንዳ

ከ3000 ዘመን በላይ አንድ አድርጎ የሠፋንን የታሪክ ውጣ ውረድ ሁሉ በሸፍጥ ተክዶ ታሪካችን የመቶ ዓመት ነው እየተባለ ይሰበካል። ከላይ የተጠቀሱትን በደሎች ታዲያ ምን እንዲሽከማቸው ነው የሚጠበቀው።

ፐርፎሬሽን 7. አካባቢው በበሽታና በርሀብ ሲጠቃ አስፈላጊው ድጋፍ አለመቅረቡ

በተከታታይ ከአሥር ዓመት በላይ እየተመነደገ ነው ተብሎ የሚሰበከው የኢኮኖሚ ዕድገት የት እንደገባ ሳይታወቅ፥ ይኸው ከዓመት ዓመት አገሪቱ ሁልጊዜም ለእርዳታ እጅዋን እንደዘረጋች ነው። መንግሥት የኢኮኖሚ ዕድገት ወሬውን እንዳያጠለሽበት በማለት ሁል ጊዜም ለሕዝብ ችግር ደራሽ ከመሆን ይልቅ ቸነፈርን መደበቅ ልምዱ አድርጎታል። እድሜ ለዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ በሌሎቹ ክልሎች ተዘዋውረው የማየት እድል ስላልተነፈጋቸው በቸነፈር ለተመታው አካባቢ እርዳታ ያቀርቡለታል። ቀደም ብለን እንደጠቀስነው የሦማሌ ክልል እንደማዕከላዊ እሥር ቤት ዝግ ነው። ሕዝቡ በቸነፈርና በኮሌራ መመታቱ ሪፖርት እየተደረገ መንግሥት ግን በግዴለሽነት ይክዳል። ወያኔ የዕርዳታ እሕልንና መድኃኒትን ሕዝብን ማንበርከኪያ አድርጎ ይጠቀምበታል። ወገን በረሀብ ሲረግፍ የህወሀት ባለሥልጣናት ሀሴትን ያደርጋሉ። ክልላዊነት ሠባዊነትን አለማስቀደሙ እሙን ቢሆንም እስከዚህ ጭራቅ ማድረጉ ግን እኔን ሲገርመኝ ይኖራል። የተገላቢጦሽ ሆኖ የነፃነት ተዋጊዎቹ ከቀለባቸው እየቀነሱ ለሕዝቡ ሲያጎርሱና መድኃኒት ሲያካፍሉ ሪፖርት እየተደረገ ነው። ለችግር ያልደርሰለትን መንግሥት የትኛው ሕዝብ ነው የኔ ብሎ የሚቀበል?

ፐርፎሬሽን 8. መንግሥት የሚያራግበው ግጭት በተለይ ከዖሮሚያ ክልል ጋር

ላለፉት 25 ዓመታት ካለማቁዋረጥ ከተነዙት የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ባሽገር፤ ህወሀት ችግር ውስጥ በገባ ቁጥር ይሁነኝ ብሎ አንዱን የህብረተሠብ ክፍል ከሌላው እያጋጫ ደም ያፋሥሣል። ተረጋግተው፥ ተስማምተው፥ ተፋቅረውና ተከባብረው ይኖሩ የነበሩ የኦጋዴንና አካባቢው ነዋሪዎች ላይ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይልን በመጠቀም ዘር ለይቶ ግድያና የሰዎችን መፈናቀል ፈፀመ። በተቻለው መጠን ግጭቱን አራገበ፤ ብሔራዊው ጦርም መሀል ገብቶ ዜጎችን እንዳይታደግ አገደ። ግድያውና ማፈናቀሉ አንዱ ዘር በሌላው ላይ የፈፀመው ጥቃት በማስመሰል አናፈሠ። የሶማሌ ልዩ ኃይል፣ አባይ ፀሐዬና ሳሞራ የኑስ ከአካባቢው በተፈናቀሉት፥ በተገደሉትና በተሰደዱት ንፁሐን ኢትዮጵያውያን ተጠያቂ ሊሆኑበት ሲገባ ዋጋ የከፈሉት ግን አወዳይ ይኖሩ የነበሩ ሌሎች ንፁኃን ኢትዮጵያውያን ናቸው።

ፍርደገምድሉ ዳኛ፥ አቶ ተምትም በተከሰሰበት ጉዳይ የሞት ቅጣት በሥቅላት እንዲፈፀምበት ይወስንበታል። ሕግ አስከባሪዎቹ ቅጣቱን ሊፈፅሙ ፍርደኛውን ወደመሥቀያው ሲያስጠጉት ቆለኛው ተምትም ከመስቀያው እንጨት በቁመት በልጦ ተገኘ። ይህ ችግር የቀረበለት ዳኛ መላ እንዲመቱ አካባቢው ያሉትን ሲያማክር፣ አቃቤ ሕጉ ተምትም ደገኛ አጭር ወንድም እንዳለው ሹክ ይላል። ዳኛው “ታዲያ ምን ትጠብቃላችሁ አምጡና አንጠልጥሉት!” ብሎ አንባረቀ። የተምትም ወንድም፥ ጉዋንጉል የደቻሣን ልጅ ለቅሶ ሊደርስ ወደ ደቻሳ ቤት ሲያቀና ሕግ አስከባሪዎቹ አግኝተውት፤ እያዳፉ ወስደው ቤተሰቡን ለመሰናበት እንኩዋን ዕድል ነፍገው፤ ጥፋቱንም ሳይነግሩት አንጠለጠሉት። የዘር ነገር ከዚህ መራራ ቀልድ ምንም አይለይም። በቃ! ይኸው በተደጋጋሚ ደርሶብን እያጣጣምነው ነው።

የህወሀት መሠሪ ተግባር በዚህ አላበቃም። ደም የለመደው የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ላሳካው ተልዕኮ ሊወደስና ሽልማት ሊለገስ ተወሰነለት። ይህ የሽልማት አሠጣጥ የበለጠ ከፋፋይና በማኅበረሰቡ ዘንድ ጊዜን ጠብቆ የሚያመረቅዝ ቁስል ይሆን ዘንድ፤ በትግራይ ሕዝብ ሥም ተደርጎ በመቶ ሺ ከጅጅጋ የተፈናቀሉትንና በገዛ አገራቸው ማረፊያ አጥተው የሚንሳፈፉትን ምንዱባን ረግጦ ተሻግሮ፤ በሌሎቹ ተፈናቃዮች ሥም ለወንበዴዎቹ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ተለገሰ።

ፖለቲካ የሚለውን ቃል ሕዝብን በማጋጨትና በማደህየት አቅም አሣጥቶ ለዘላለም መግዛት የሚል ትርጉም ሠጥቶ ያለዕረፍት እንቅልፍ አጥቶ የሚባጀው ወያኔ፤ የኢትዮጵያዊነት ማጠንጠኛ ዕምብርት የሆነውን ታላቁን የትግራይ ሕዝብ የዕኩይ ተግባሩ ተባባሪ ለማስመሰል የሚያደርገው ጥረት ሁልጊዜም ያሣዝናል። ህወሀት የትግራይን ሕዝብ መጠቀሚያ ያደርገዋል እንጂ ጨርሶም አይወደውም። አዳፍኔ ፍቅር የለውም። ካልታመንኩኝ፣ ፕሮፈሠር መስፍንን ምሥክርነት እጠራለሁ። የወጋ ቢረሳ የተወጋ… እንዲሉ ነውና የሐውዜንን ዕልቂት እኛም አንረሳው፤ ልጆቻችንም ሳይረሱት ለልጆቻቸው እንዲያወርሱ አሳስበን የምናስተላልፈው ታሪክ ነው። ቀለም የቀመሱ ወጣቶች ጸሀይና ዝናብ በገበያ ቀናት ለሚፈራረቅባቸው ወላጆቻቸው መፍትሔ ፍለጋ የገበያ አዳራሽ ለመሥራት ጥረት ያደርጋሉ እንጂ እንደ ብቅል ሜዳላይ ጢም ብለው ሲሰጡና ገበያው ሲደራ ጠብቀው የቪዲዮ ካሜራዎችን አስተካክለው ቦምብ ጣይ አይሮፕላን በእጅ አዙር አያስልኩም። የሐውዜን ነዋሪን እልቂት የምንዘነጋው ሣይሆን ነፃ ስንወጣ በየዓመቱ ከየካቲት 12 ዕልቂት ዕኩል የምንዘክረው ቀን ነው። በጠይም ፋሽሥቶች መፈፀሙ ጥፋቱን አያሣንሠውም።  ግን ለዚህ እርኩስ ምግባር የዋለ መሠሪ ዐዕምሮ በበጎ ነገር ላይ ቢውል የአካባቢውን ድንጋይ ሁሉ ወደ ዳቦ በቀየረው ነበር ብየ ሁልጊዜም ሲቆጨኝ ይኖራል።

መፍትሔውስ

በምርጫ 97 የምርጫ ውድድርና በምርጫው ማግሥት የተደረገውን የሕዝብ ድምፅ ዘረፋ ተከትሎ በነበረው የፍጥጫ ወቅት ገዢው ፓርቲ እጅግ የዘቀጠና ኃላፊነት የጎደለው እንቅስቃሤ በሚያደርግበት ወቅት፤ ተቃዋሚዎች ነበሩ ፍጥጫው ወደ ዕልቂት ከሚያመራ ይልቅ ከሕዝብ ያገኙትን ድምፅ መደራደሪያ እስከማድርግ ሄደው የነበሩት። ህወሃትማ እንተርሐምዌ ብሎ የሩዋንዳ ዕልቂት ወደ ኢትዮጵያ እንዲዘልቅ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኩል ቪዛ ሠጥቶ ነበር። ህወሀትማ በትግሬ ወደ መቀሌ ንብረት ወደ ቀበሌ ተረት ሊያጫርሰን ሠይፉን ስሎ ነበር። ህወሀትማ በቅርብ ጊዜ ታሪኳ ራስዋን ከመከላከል ውጪ በምንም ጉዳይ በሌሎች አገሮች ጣልቃ ገብታ የማታቀውን አገር ሠራዊትዋ የሉአላዊ አገርን ግዛት እንዲደፍር አሥደረገ። የወገኖቻችንም አስከሬን በሞቃዲሾ ጎዳናዎች ላይ አስጎተተ። ለህወሀት የአሜሪካውያን ከሚጎተት ተሽሎታል። ምን ያህል ነው የሞተብን ለመሆኑ ለሚለው ጥያቄ እንኩዋን ቁጥሩን ማወቁ ምንም አይጠቅማችሁም ነበር መልሡ። የኢትዮጵያ እናቶች ፅናቱን ይስጥችሁ።

በሠለጠኑት አገሮች የምንኖር ዜጎች መንግሥት ምን ያህል ኃላፊነትን እንደሚሸከም በውል የምንገነዘበው ነው። አይደለም የሚከተለው ፖሊሲ ለወለዳቸው ችግሮች በተፈጥሮ ለደረሱ ጉዳቶች እንኩዋን በቂ ዝግጅት ባለማድረጉ መንግሥት ሲብጠለጥል በየጊዜው የምናየው ነው። በአገራችን ግን ሁኔታዎች ተገለባብጠው ጉልበተኛው፥ ትልቁ፥ ከሕዝብ ግብር የሚሰበስበው መንግሥት ከቀን ቀን አገር የሚያፈርሥ፥ ሕዝብን ለዕልቂት የሚዳርግ ተግባሮችን ሢፈፅም፤ በአንፃሩ በህቡዕ የሚንቀሳቀሱት፥ በዕርጥባን የሚተዳደሩት፥ ከሕሊናቸው አስገዳጅነት ውጪ ከማንም አደራ ያልተቀበሉት ተቃዋሚዎች ሆነዋል ዋና ዓላማቸውን አልፎ አልፎም ቢሆን እያሳረፉ አገሪቱ እንዳትበታተን፥ የሕዝቡ ደሕንነት እንዲጠበቅ ዐቅማቸው ከሚፈቅደው በላይ የሚዋጁት። የእያንዳንዱ ክልል ችግር የኢትዮጵያ፥ የኢትዮጵያ ችግር የክልሎቹ በመሆኑ መፍትሄው በአገር ደረጃ መፈለግ አለበት። ወደመፍትሄው አየተንደረደርን መሆኑን እድሜ ለኦዴፍ፥ እድሜ ለሲዳማ ንቅናቄ፥ እድሜ ለአፋር ሕዝብ ድርጅት፥ በመጨረሻም አቋሙን አለዝቦ በኢትዮጵያ ጠላቶች ላይ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ክንዱን ሊያነሳ ቃል ለገባው እድሜ ለኦብነግ ኢትዮጵያ የልጆችዋ ሠቆቃ የሚያበቃበት ጭላንጭል እየታየ ይመስላል።

የአርበኞች ግንቦት ሠባት መሪዎች በበረሀ ጋራውን ወተው ሸንተረሩን ወርደው ቁሩንና ሀሩሩን ተቁዋቁመው ከሚያካሂዱት የጦር ትንቅንቅ ባሻገር ለዲፕሎማሲ ለገቢ ማሰባሰብና ለፖሎቲካ ሥራ ያለዕረፍት ሕይወታቸውን ለአደጋ እያጋለጡ ወዲያ ወዲህ ሲሉ፤ ራስ ኃይለሥላሤ ጉግሣ መለስ ዜናዊንና ህወሐቶችን ወልደው በመተካታቸው ቢያሠቅቁንም፤ አቡነ ጴጥሮሥም አልመከኑም ብለን እንድንፅናና ያደርጉናል። ከወያኔ ጥይት በማይተናነስ ሁኔታ ከሌሎች ተቃዋሚ ነን ባዮች እንደ ዝናብ ለሚወርድባቸው ሽሙጥ፥ ኤርትራ እንደ መግቢያና መውጫ በመጠቀማቸው ብቻ በከሃዲነት ሲወነጀሉ፤ ለምን ከጎሣ ድርጅት ጋር ተወያዩ ተብለው እራሣቸው በጎሣ እየተደራጁ ባሉ አካላት ሲብጠለጠሉ፥ ገንዘብ ከደጋፊ መሰብሰብ ነው ሥራቸው ተብለው ሲወቀሱ፤ የአማራ ጠላት ተደርገው ሲፈረጁ፤ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው አገርን ለማዳን መትጋታቸውን እናደንቃለን። ለሣምሦን የሠጠውን ጉልበት እግዚአብሔር ለናንተም እንዳይነፍጋችሁ እንጸልያለን። ታዲያ አንድነታችሁን አደራ ጠብቁት ፀጉራችሁ እሡ ነውና ብለን እንመክራለን።