ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ሆይ! በናዚ ሐኪሞች የደም ታሪክ ከመዘፈቅ ታቀቡ (በላይነህ አባተ)

ህሊናው ባሸነፈው ሐኪም አማካኝነት የሁለት መቶ አምሳ ልማታዊ ሐኪሞች ያየር ባየር ንግድ እንደገና አደባባይ ወጥቷል፡፡ ያየር ባየሩን ንግድ ከምድር ለማውረድ ከዚህ ህሊናው ካሸነፈው ጎበዝ በቀር ሁሉም ልማታዊ ሐኪሞች ኢትዮጵያውያኖች በወንጀል የሚከሱትን ቴድሮስ አድሃኖምን እሽኮኮ ተሸክመው ከወንበር ለመስቀል በውድም ሆነ በግድ ተስማምተዋል፡፡[1] ይህ ያየር ባየር ንግድና ወንጀለኛን በክትፎ ባበጠ ጫንቃ እሽኮኮ መሸከም የናዚ ሐኪሞችን ታሪክ አስታውሶኛል፡፡ በዘረኝነት በተገነባው የናዚ አገዛዝ ዘመን ከግማሽ በላይ የጀርመን ሐኪሞች ከሂትለር ጎን ተሰልፈው ነበር፡፡ [Nazi doctors list 2-4]. እንዲያውም ዶክተር ኢርነስት የተባሉ አይሁዳዊ ያልሆኑ ተመራማሪ “ያለ ሐኪሞች ተሳትፎ ሆሊኮስት እሚባለው የአይሁዶች እልቂት አይሳካም ነበር” ሲሉ በታወቀው የአለም አቀፍ የበሽታዎች ስርጪት መጽሔት (International Journal of Epidemiology) እ.ኤ.አ. በ2001 ዓ.ም ጽፈዋል፡፡ [5]

እንዳገራቸው ባህልና ሥርዓተ- አምልኮት ሐኪሞች የሚገቡት “ሂፖክራቲስ ኦዝ”[6] እሚባለው ቃል ኪዳን “ሥራዬን በንጹሕነትና በቅድስና ሳከናውን እኖራለሁ፤ ከአጭበርባሪነትና ሙስናዊ ተግባራት እቆጠባለሁ …” የሚሉ ፅንሰ-ሐሳቦች ይገኙበታል፡፡ እነዚህንና ሌሎችንም የቃል ኪዳን ፅንሰ-ሐሳቦች ብቻ ሳይሆን የሰውነትን ባህሪም ቡጭቅጭቅ አድርገው የበሉ ሐኪሞች ሂትለር እንደ መለስ ዜናዊ “ያይኑ ቀለም አላማረኝም” ያለውን ሁሉ አስፈጅተዋል፡፡ ሐኪሞቹ ሕዝብን ያስፈጁት ለናዚ አገዛዝ የሐሳብ፣ የመንፈስና የቁሳቁስ ድጋፍ ከመስጠት በተጨማሪ ሂትለር እሚጠላቸውን ዘሮች በማምከን፣ በጀርም በመበከል፣ በጋስ በማፈን፣ ጣጣቴ በመተኮስና በሌሎችም መንገዶች ሕዝብን በማሰቃየት ነበር፡፡ [7,8]

ከናዚው እልቂት ከአምሳ ዓመታት በኋላ በዘርኝነት ቦንብ የተገነባ አገዛዝ በኢትዮጵያ ተዘርግቷል፡፡ ይህ በዘርኝነት ቦንብ የተገነባ አገዛዝም በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በኦጋዴን፣ በጋምቤላ፣ በአሶሳ፣ በመተከል፣ በአምቦ፣ በወልቃይት፣ በሁመራ፣ በጉራ ፈርዳ፣ በአፋር፣ በሰቆጣ፣ በኮንሶ፣ በወለጋ፣ በሲዳሞና ሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች በዘራቸው ወይም በቋንቋቸው ምክንያት ዜጎች እንዲያልቁ አድርጓል፡፡ የዚህ እልቂት መረጃም በመላው የኢትዮጵያ ምድር ተቀብሮ ይገኛል፡፡ ከተቀበረው መረጃ ኢምንቱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ ጪሮ አውጥቷል፡፡ [8] እንደ ሂዩማን ራይትስ ዋች[9]፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል[10]፣ ፍሪደም ዋች[11] የመሳሰሉት ድርጅቶችም ኢምንቱን መዝግበዋል፡፡ የዘር ማጥፋትን ወንጀል የሚከታተለው ጀኖሳድ ዋችም ነፍሰ-ገድዮች ላለም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡[12] የጀርመኑ ዘረኛ አገዛዝ አይሁዶችን እንዳመከነው የኢትዮጵያው ዘረኛ አገዛዝም አማሮችን በማምከን ወንጀል ተከሷል፡፡ [14-16] አብዛኛው የዘረኝነት እልቂት መረጃ ግን ቆፍሮ እሚያወጣ ጋዜጠኛ፣ የቅሬት አካል ባለሙያ፣ የታሪክ ተመራማሪ፣ የሕግ  ባለሙያና ህሊናውን ያልገፈፈ ዜጋ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ዘርን ወይም ቋንቋን መሰረት አድርጎ በተለያዩ ዘዴዎች ያለቀው ሕዝብ ወደ ፊት በትክክል ሲቆጠር በሆሊኮስት ካለቀው ሕዝብ እንደሚበልጥ ይገመታል፡፡

ልማታዊ ሐኪሞች ሆይ! በጀርመን ሕዝብ  ከበረት ተከማችቶ እንደተጨፈጨፈው በኢትዮጵያም ሕዝብ በክልል ታጉሮ እየተጨፈጨፈ መሆኑን የምትገነዘቡ ይመስለኛል፡፡ ካልተገነዘባችሁም ጭፍጨፋውን ላለመረዳት አውቃችሁ ተኝታችኋል፡፡ ተገንዝባችሁ ጪጭ ካላችሁም ሳትሞቱ በሽንፍላ ከፈን ተከፍናችኋል፡፡ ጭፍጨፋ እንደሌለ የምትሰብኩትም እንደ መለስ ዜናዊና ቴድሮስ አድሃኖም ዓይናችሁን በጨው ታጥባችኋል፡፡ ዓይናችሁን በጨው የታጠባችሁት ሳይቀር በጮሌነት “አገዛዙ በድሎናል” በሚል ማመልከቻ የእንጀራ መጉረሻ መኖሪያ ፈቃዳችሁን በሰሜን አሜሪካ አግኝታችኋል፡፡ የማመልከቻችሁ ቀለም ሳይደርቅ በደሉን ካላችኋቸው ዘረኛ ነፍሰ-ገዳዮች ጀርባ በልማታዊ ሐኪምነት ቆማችሁ የሂፖክሪትስን መሐላ እንደ ናዚ ሐኪሞች ዘንችራችኋል፡፡

የሂፖክሪትስን መሐላ ከዘነቸራችሁት ሐኪሞች አንዳንዶቻችሁን ለምን ድሃ ከፍሎ ሊታከምበት የማይችል ዘመናዊ ሆስፒታል ከነፍሰ-ገዳዮች እግር እየወደቃችሁ እንደምትገነቡ ስንጠይቃችሁ “ውጪ አገር እየሄዱ የሚታከሙትን ከበርቴዎች እዚያው ለማስቀረት” እሚል መልስ ሰጥታችኋል፡፡ ውጪ አገር እሚታከሙት ከበርቴዎች ደግሞ ነፍሰ-ገዳይዎች ወይም ከነፍሰ-ገዳይዎች ጋር የተሻረኩ ቱጃሮች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ነፍሰ-ገዳይዎችና ከነፍሰ-ገዳይ የተሻረኩ ቱጃሮች በድሃ ሥም የተረጠቡትንና ከድሃ ደም ሥር የመጠጡትን የደም ገንዘብ ለመካፍል ኪሳችሁን እንደ ካናዳ ኬሻ ከፍታችኋል፡፡ ከነፍሰ-ገዳዮች እየተዳራችሁ በጥይትና በግርፋት የሚያልቁትን ድሆች ረስታችኋል፡፡ ከአፋቸው እየሞለቀቁ በእንቁላልና በፍርፍር ያስተማሯችሁን እንጀራ ጋጋሪዋን ወይዘሮ ስለእናትን፣ እርፍ ጨባጩን አቶ አድማሱን፣ አምባሻ ጋጋሪዋን ወይዘሮ ሀዳስን፣ እንጨት ለቃሚዋን ወይዘሮ ዘይነባን፣ ቡና ለቃሚውን አቶ ረጋሳን፣ ቆሎ ሻጯን ወይዘሮ ሀሊማን፣ ጨጨብሳ አንጓቿን ወይዘሮ ጫልቱን፣ እንሰት ላጊውን አቶ ዘበርጋን፣ ጪቃ አቡኪውን አቶ ደሌቦን፣ ሸማ ሰሪውን አቶ ጫቦን ከድታችኋል፡፡

የናዚ ሐኪሞች የዘረኛውን የሂትለርን ጀኔራሎች እርካብ ሆነው ከፈረስ እንደሰቀሉ እናንተም በዘር  ከተለከፈው “መለስ ዜናዊ ጋር መስራት መባርክ ነው” ያለውን ቴድሮስ አድሐኖምን ባርጩማ ሆናችሁ ከወንበር ለመስቀል ትከሻችሁን ዝቅ አድርጋችሁ አጎብድዳችኋል፡፡ በነቴድሮስ አድሃኖም ጠባቂዎች ጭካኔ እየፈሰሰ ያለውን የአምቦዋን፣ የወልቃይቷን፣ የሁመራዋን፣ የጋንቤላንዋን፣ የወለጋዋን፣ የኮንሶንዋን፣ የኦጋዴኗንና የመተከሏን እናት እንባ ወደ ደም ቀይራችሁታል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሕክምና ጥበባቸውን የወረሳችሁትን ዳሩ ግን በቂ ሕክምና ተነፍጓቸው ያለፉትን ፕሮፌሰር አስራትን መቃብር ውስጥ በጦር ወግታችኋል፡፡ በነቴድሮስ ወታደሮች በመላ አገሪቱ በተረሸኑት ዜጎች ቀልዳችኋል፡፡

ሂትለርና አብረውት ዘግናኙን ወንጀል የፈጠሙት ሐኪሞች በስብሰው ፈራርሰዋል፡፡ በአድርባይነትና በሆዳምነት ድምጣቸውን አጥፍተው የነበሩት ሐኪሞችም ትቢያ ሆነዋል፡፡ እርግጥ ነው ስስታሙ አንጎላቸው፣ ጨካኙ እጃቸው፣ ሰፊው ከርሳቸውና አጎብዳጁ ወገባቸው ከገደል እንደ ወደቀ ሸክላ  ብትንትን ብሏል፡፡ አይሁዶችን በማምከን ሥራ ተጠምደው የነበሩት እንደነ ዶክተር ራይተር ያሉ ሐኪሞችም ከሞቱ በኋላ ክብራቸው ተገፏል፡፡ [17] ዘግናኝ ታሪካቸው ግን ዘመን በገፋ ቁጥር የበለጠ እየጎላና እየተንቀለቀለ ይሄዳል፡፡ እንደ ናዚ ሐኪሞች ሁሉ የእኔና የእናንተም ስስታም አንጎል፣ ሞጭላፊ እጅ፣ ቀላዋጭ ዓይን፣ ሰፊ ከርስ፣ አዙሮ እማያይ አንገትና አጎብዳጅ ወገብ ነገ ተበጣጥሶ ትቢያ ይሆናል፡፡ የማይበጣጠሰውና ትቢያ እማይሆነው እንዲያውም ዘመን በገፋ ቁጥር እየጎላ እሚሄደው ታሪካችን ይሆናል፡፡ እኛ እየተሽሎኮሎክን ያመለጥን ብንመስልም ታሪክ ድምጡን አጥፍቶ በመመዝገብና በመጠረዝ ላይ ይገኛል፡፡ በታሪክ መዝጋቢነትም  እንዳለመታደል እኛም እንደ ጀርመኖች የወንጀለኞችና ያልተባረኩ ሐኪሞች ዝርዝር ይኖረናል፡፡

ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ሆይ! ሕዝብን ደም ካስለቀሱ ወንጀለኞች ጋር መሽኮርመሙ ይቅርባችሁ፡፡ ስስትና አድርባይነት የሚያብከነክነውን ሥጋችሁን ለማርካት ስትሉ እባካችሁ ዓይናችሁን ጨፍናችሁ በናዚ ሐኪሞች የደም ታሪክ ከመዘፈቅ ታቀቡ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

ዋቢ

 1. ቃለ መጠይቅ ከዶክተር ግርማ መኮንን ጋር http://ethsat.com/esat-radio-wed-15-june-2016/ (Last accessed on June 18, 2016)
 2. List of Nazi MDS, https://en.wikipedia.org/wiki/List_of_Nazi_doctors (Last acessed on June 18, 2016)
 3. The Nazi Docotrs: http://www.auschwitz.dk/doctors.htm (Last accessed on June 18, 2016)
 4. Nazi doctors: http://faculty.webster.edu/woolflm/nazidocsandothers.html ((Last accessed on June 18, 2016)
 5. Earnest: The Third Reich—German physicians between resistance and participation, Int. J. Epidemiol.(2001)30 (1):37-42.doi: 10.1093/ije/30.1.37  http://ije.oxfordjournals.org/content/30/1/37.full
 6. Hippocratic Oath (400 BC) as translated by by Francis Adams (1849)http://www.britannica.com/topic/Hippocratic-oath ((Last accessed on June 18, 2016)
 7. The Nazi Doctors and the Nuremberg Code: Human Rights in Human Experimentation” Oxford University Press. May 7, 1992. Page 19 ((Last accessed on June 18, 2016)
 8. 13. Exhibition Examines Scientists’ Complicity In Nazi-Era Atrocities” The New York Times. Author, Warren E. Leary. November 10, 1992 ((Last accessed on June 18, 2016) (Last accessed on June 18, 2016)
 9. ሰብአዊ መብት ጉባኤ ሪፖርት 2008 ዓ.ም. http://ehrco.org/wp-content/uploads/2016/06/HRCO-141st-Special-Report-Amharic-Sene-01-2008.pdf (Last accessed on June 18, 2016)
 10. Protest Crack Down killed hundreds, Ethiopia, Human Rights Watch https://www.hrw.org/news/2016/06/15/ethiopia-protest-crackdown-killed-hundreds (Last accessed on June 18, 2016)
 11. Extrajudicial executions, Arbitray arests and detntions Amnesty International

 https://www.amnesty.org/en/countries/africa/ethiopia/report-ethiopia/ (Last accessed on June 18, 2016)

 1. Ethiopia, Police Open fire on Protesters https://freedomhouse.org/article/ethiopia-police-open-fire-protesters (Last accessed on June 18, 2016)

13. Genocide watch documents on Ethiopia     http://www.genocidewatch.org/ethiopia.html (Last accessed on June 18, 2016)

 1. Three million Amhars Missing, Berhanu Abegaz https://www.youtube.com/watch?v=3-g-YWYBdbM ((Last accessed on June 18, 2016)
 2. Three Million Amara are Missing: An Analysis based on the 1994 and the 2007 Ethiopian Population Censuses,Berhanu Abegaz, http://ethiomedia.com/101facts/45139 ((Last accessed on June 18, 2016)
 3. Human right violation of Amharas Muluken Tesfaw http://video.ethsat.com/?p=24983 ((Last accessed on June 19, 2016)
 4. Experts Re-Examine Dr. Reiter, His Syndrome and His Nazi Past

https://partners.nytimes.com/library/national/science/health/030700hth-doctors.html ((Last accessed on June 18, 2016)

ሰኔ ሁለት ሺ ስምንት ዓ. ም.