አቶ ለማ መገርሳን የመገልበጥ እንዲሁም ህዝብን የማጫረስ ሴራን የሚያውጠነጥኑት ከፍተኛ ባለስልጣናት ስም ዝርዝር በመረጃ መረጋገጡ ተሰማ

ምስል ከፋይል

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ያለውን እርስ በእርስ የማጋጨት ሴራ የአገዛዙ የስለላና የደህንነት  ተቋም በበላይነት እየመራና እያቀነባበረው እንደሚገኝ የሚያሳይ በቂ ማስረጃ እንዳለ ተገለጸ።

በህውሃት የበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት በስልጣን ላይ ለመቆየት ከሚጠቀምባቸው ቁልፍ ስልቶች መካከል በዋናነት የሚነገርለት ዘርን ከዘር የማጋጨት ሂደት በብዛት በአማራ በኦሮሞና በሶማሊያ ተወላጆች ላይ ተግባራዊ ማድረጉን ቀጥሏል።

የሶማሌና የኦሮሚያ ወገኖቻችን እርስ በእርሳቸው እንዲጋጩ የተሰራው ሴራ ለመቶዎች ህይወት ማለፍ እንዲሁም ለበርካታ መፈናቀል ምክንያት መሆኑ ይታወሳል።

በኢሉባቦር በአማራና በኦሮሞ ዜጎቻችን መካከል ግጭት እንዲፈጠር የጠነሰሰው አገዛዙ በስልጣን ላይ ለመቆየት ከሚተማመንባቸው ተቋማት መካከል የሆነው የብሄራዊ ደህንነት መስሪያ ቤትን በመጠቀም እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።

በአቶ ጌታቸው አሰፋ የሚመራው የደህንነት መስሪያ ቤት ኢትዮጵያውያኖች እርስ በእርሳቸው በጥላቻ ተነካክሰው እንዲጫረሱ እያደረገ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳላቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በላስ ቬጋስ ለህዝብ ባደረጉት ንግግር በይፋ ተናግረዋል።

ይህን ንጹሃን ወገኖቻችንን እርስ በእርስ የማባላት ተልእኮን ከብሄራዊ ደህንነት ሃላፊ ከሆኑት ከአቶ ጌታቸው ቀጥታ ትእዛዝን በመቀበል ተግባራዊ እንዲሆን የማድረጉ ሃላፊነትን ወስደው የሚንቀሳቀሱት ባለስልጣን የአገር ውስጥ ደህንነት ዋና መምሪያ ሃላፊ የሆኑት አቶ አማኑኤል ኪሮስ እንደሆኑ ለታዳሚው አሳውቀዋል።

የብሄሮችን ግጭት  በአገሪቷ እንዲቀጣጠል የሚደረገውን ሴራ በማማከር እንዲሁም በማስፈጸም አቶ አማኑኤል ኪሮስን እየረዱ ያሉ ሌላኛው ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣን አቶ ደርበው ደመላሽ እንደሆኑም ተናግረዋል።

በአገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን ያላቸው አቶ ተስፋዬ ኡርጌ እና አቶ አዲሱ በዳዳ በኢሉባቦር የደረሰውን ግጭት በማቀነባበርና በበላይነት በመምራት መሳተፋቸውን በመረጃ ማረጋገጣቸውን ፕሮፌሰሩ በተጨማሪ ገልጸዋል። እነዚህ ሁለት ከፍተኛ ባለስልጣናት በኦሮሚያ ክልል የደህንነትና የስለላ ስራን በጥብቅ የሚከታተሉና የሃላፊነት ደረጃን ተቆናጥጠው የሚመሩ መሆናቸውም ታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል የአስተዳደርና የጸጥታ ሃላፊ ሆኖ የሚያገለግሉት ረዳት ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረ መስቀል  ከላይ ከተጠቀሱት ባለስልጣናት በተጫማሪ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆችን የማጋጨት ተልእኮን ተግባራዊ በማድረግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኝም ተነግሯል።

አቶ አዲሱ ገዳዳ እና አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ከኦሮሚያ የገጠር መንገዶች መስሪያ ቤት በሃላፊነት ከሚሰሩ ከአቶ ጀማል አባሶ ጋር በመሆን በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራውን የኦሮሚያ አስተዳደርን ለመገልበጥና ለመለወጥ እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም ተገልጿል።