የኢትዮጵያ መንግስት በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቹ ወደ ሶማሊያ መግባታቸውን አሳወቀ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

ባሳለፍነው ኦክቶበር 14 ቀን 2017እኤአ በሶማሊያ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ የሶማሊያ መንግስት ሽብርተኛውን  አልሸባብን ለመዋጋት የጎረቤት አገራትን እርዳታ ጠይቋል።

አልሸባብን ለመዋጋት ከአጎራባቾች አፍሪቃውያን ወታደራዊ እርዳታ በተጨማሪ የአሜሪካ መከላከያ በሰው አልባ የጦር ጀት የሚያደርገው እገዛ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበታል።

በአገሪቱ ውስጥ በተስፋፋው ከፍተኛ የህዝብ እምቢተኝነትና ተቃውሞ ምክንያት ከዩናይትድ ስቴትስና ከምእራብዋያኑ ጋር ቅራኔ ውስጥ የገባው የኢትዮጵያ መንግስት ይህን የሻከረውን ግንኙነት ለማለሳለስ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቹን ወደ ሶማሊያ ሰድዷል።

በከባድ ተሽከርካሪዎች ተጭነው ወደ ደቡባዊ ሶማሊያ ከዘለቁት የኢትዮጵያ ወታደሮች በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታንኮችና ከባባድ የጦር መሳሪያዎችም ሲገቡ እንደተመለከቱ የዶሎ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የሆኑት አቶ ወርቅነህ ገበየው ከፍተኛ ቁጥር ወታደሮች በታንኮች ታጅበው ወደ ሶማሊያ መግባታቸውን አረጋግጠዋል።

ይህ የኢትዮጵያ መንግስት በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ለጦር ፍጆታ ወደ ሶማሊያ የመላክ ውሳኔ ምእራብውያኑንና አሜሪካንን የሚያስደስት ሲሆን በአለም አቀፍ ሚዲያዎችም በሰፊው እየተዘገበ ይገኛል።