አረና ትግራይ በመቀሌ ባደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ወታደሮች ህዝቡን አስፈራርተውብኛል በማለት ቅራኔውን አሰማ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

የአረና ትግራይ ፓርቲ በመቀሌ ከተማ መንግስትን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጉ ታወቀ። ፓርቲው የጠራውን ሰልፍ የመቀሌ አስተዳደር ፍቃድ እንዳልሰጠውም ተገልጿል።

በሰልፉ ላይ የመቀሌ ነዋሪዎች ወደ አደባባይ እንዳይወጡ በቀበሌዎች የተደራጁ ግብረሃይሎች ቤት ለቤት በመዞር ሲያስፈራሩ እንደነበሩም ተዘግቧል።

ሰልፉ ከመካሄዱ በፊት በታክሲዎችና በየመንገዶች ድንገተኛ ፍተሻዎች ሲደረጉ፣ እንዲሁም ወታደሮች በድምጽ ማጉያ በየመንገዱ ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ እንደነበሩም ተገልጿል።

በመቀሌ በተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፉት በእጅ የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሆኑ፤ በየመንገዱ ዳር ሆነው ሰልፉን ሲመለከቱና ፎቶ ሲያነሱ የነበሩ ነዋሪዎች በርካታ እንደነበሩም ታውቋል።

የሰልፉ ዋና አላማ  በመቱ፣ በኢሊባቡር እንዲሁም በኦሮሚያና በአማራ ክልል የሚደረጉትን ግድያ በመቃወም እንደሆነ ፓርቲው አሳውቋል።

በቁጥር እጅግ ጥቂት ግለሰቦች ፓርቲው በመቀሌ በጠራው ሰልፍ ላይ ቢሳተፉም አገዛዙ ከፍተኛ ሃይል ያከማቸበት ከተማ ላይ ስርአቱን ለመቃወም በድፍረት መውጣታቸው ጥሩ ጅማሬ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

እንኳን አገዛዙ የጦር ሃይሉን ያጨቀበት እንደ መቀሌ ያለ ከተማ ላይ ቀርቶ ነጻነት በአለበት የምእራባውያኑ አገራት ያሉ ሰዎች አገዛዙ በንጹሃን ኢትዮጵያውያኖች ላይ የሚያደርገውን ግድያና ግፍ ለመቃወም ወደ አደባባይ ለመውጣት ምን ያህል ፍርሃት እንዳለባቸው እያነጻጸሩ አስተያየታቸውን በሶሻል ሚዲያ እየሰጡ የሚገኙም ተበራክተዋል።

በአንጻሩ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች እንዲህ አይነቱ አገዛዙን የመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ እንኳን በሰላም ሊካሄድ እንደውም ደም ሳይፈስና ህይወት ሳይጠፋ እንደማይበተን አስተያየታቸውን የሚሰጡም ግለሰቦች ተገኝተዋል።