ፓስፖርትና ቪዛ መከልከሉ በርካታ ዜጎቻችንን በኬኒያ ለእስርና ስቃይ እያበቃ ነው ተባለ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የኬኒያ ፖሊስ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገሬ የገቡ ያላቸውን 132 ኢትዮጵያውያንን ማሰሩን አስታወቀ።

በኬኒያ ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት 132ቱ ኢትዮጵያውያን በአንድ ቤት ውስጥ ትፍግፍግ ባለ ሁኔታ እንዳሉ የታያዙ ሲሆን ሁሉም ምንም ዓይነት የማንነት መግለጫ ዶክመንት እንደሌላቸው ፖሊስ አስታውቋል።

በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ/ተጓዥ ዘንድ እንደ የተስፋይቱ ምድር ተደርጋ የምትታወቀው ደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያውያኑ የጉዞ መጨረሻ እንደሆነች የታወቀ ሲሆን በተለምዶ አጠራር ደላላዎች/አሸጋጋሪዎች በሚባሉት ሰዎች መሪነት በአንድ ቤት ውስጥ ተፋፍገው እንዲቀመጡ መደረጋቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

በኢትዮጵያና ኬኒያ የሁለቲዮሽ ስምምነት መሰረት የሁለቱም ሀገር ዜጎች ወደ ፈለጉበት ሀገር [ወደ ኬኒያ ወይም ወደ ኢትዮጵያ] ለመጓዝ ያለምንም የቪዛ ጥያቄ በነጻ መግባት እንደሚችሉ የሚደነግግ ሲሆን የመግቢያ ቪዛ ብቻ በአየር ማረፊያ ወይም በቦርደር ላይ ይሰጣቸዋል ቢልም በኬኒያ በኩል ግን በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በሕገ-ወጥነት ሰበብ ሲያስሩና ሲያንገላቱ ማየት የተለመደ ተግባር ሆኗል።

በናይሮቢ ያለው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በበኩሉ ዜጎቹን ለመከላከል ከሚያደርገው አነስተኛ ጥረት በተጨማሪ በሚጐዳበት ተግባር ላይ  መሳተፉ በይበልጥ ይታወቃል። በሕገ-ወጥነት በኬኒያ ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ኢትዮጵያውያን እጣፈንታ በፍርድ ቤት የሚወሰን ሲሆን የ20 ሺህ ሽልንግ [$200] ቅጣትና ወደ ሀገራቸው በግድ መመለስ ውሳኔ እንደሚጠብቃቸውም ይታመናል።

ዛሬ ከተያዙት 132ቱ ኢትዮጵያውያን ሌላ ከሳምንታት በፊት 67 ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ ሁኔታ ተይዘው የተፈረደባቸው ሲሆን ለኢትዮጵያውያኑ በጎረቤት ሀገር ውስጥ መጉላላትና መሰቃየት ግንባር ቀደም ተጠያቂው ሃይል የኢትዮጵያ መንግስት እንደሆነ በናይሮቢ ያሉ የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ኢትዮጵያውያኑ በተለይም የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ከሆኑት የወላይታ፣ ከምባታ፣ ሀዲያና ሲዳማ ዞን ተወላጆች መንግስት ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን በማገድ ፓስፖርትና የመውጫ ቪዛ ስለማይሰጣቸው በሀገራቸው ባለው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግር ምክንያት መኖር ያልቻሉት የእነዚህ አካባቢ ተወላጆች ያለበቂ ዶክመንት ከሀገራቸው ለመሰደድ በመገደዳቸው በሰው ሀገር ውስጥ ሕገ ወጥ እየተባሉ ለእስርና ለአሸጋጋሪዎች ሰለባ ለመሆን እንደቻሉ መረዳት ተችሏል።

በሀገራቸው መንግስት የዜግነት መብታቸውን ፓስፖርትና የመውጪያ ቪዛ በመከልከላቸው የነጻ ቪዛ ስርዓትን ለኢትዮጵያውያን ባላስቀመጠችው ኬኒያ እንኹአን ሳይቀር በሕገ-ወጥነት እየተያዙ ሲሰቃዩ ለማየት ተችሏል።

በሞያሌ ያለው የኢትዮጵያ ኢምግሬሽን ከአንድ የደቡብ ክልል ተወላጅ ከ8,000-12,000 ሺህ ብር በመቀበል በነጻ መስጠት የሚገባውን የመውጪ ቪዛ እንደሚሰጥ መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን በአብዛኛው ግዜ ግን ይህንን አገልግሎት የደቡብ ክልል ተወላጆች ከእነ አካቴው የማያገኙበት ሁኔታ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ኢትዮጵያውያኑ ከሀገራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ለመውጣት ያስገደዳቸው የስርዓቱ በቪዛና ፓስፖርት ላይ ያደረገው ማእቀብ እና በተጓዳኝ ደግሞ ያሉበት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግር በሀገር የማያስቀምጥ ከመሆኑ የተነሳ ረዥሙን ጉዞ ያለዶክመንት ለመጓዝ በመገደዳቸው በኬኒያ፣ ታንዛኒያ፣ ሞዛምቢክና ማላዊ እስር ቤቶች ውስጥ በመቶና በሺህ የሚቆጠሩ እንዲማቅቁ ተደርገዋል።

የአዲስ አበባው ስርዓት ለኢትዮጵያውያኑ ፓስፖርትና ቪዛ መከልከሉን ከአደገኛው የደቡብ አፍሪካ ጉዞ በማስቀረት ለደህንነታቸው ስል ያደረኩት ነው ቢልም ድርጊቱ ግን ኢትዮጵያውያኑን ይበልጥ አደገኛ በሆነው ለህገ ወጥነት ጉዞና ለመጥፎ አሸጋጋሪዎች እንደዳረጋቸው ነው እንጂ ሲከላከልላቸው እየታየ አይደለም።

የኬኒያ ፖሊስ በተለይም በሞያሌ ኬኒያ ኢምግሬሽን ያለው ክፍል ይህንን መረጃ ስለሚያውቅ የመውጪያ ቪዛ እና ፓስፖርት የሌላቸውን ኢትዮጵያውያንን በማሳደድ የገቢ ምንጩ እንዳደረጋቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በናይሮቢ ያለው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በስደተኛው ውስጥ ሽብርና ፍርሃት ለመርጨት የሚያስችለውን ሃይልና አቅም በአደጋ ላይ የወድቁ ኢትዮጵያውያንን በማዳን ደረጃ አንዴም ሲጠቀምበት እንዳልታየ በናይሮቢ ያሉ ኢትዮጵያውያን ይናገራሉ።

ዛሬ የተያዙት 132ቱ ኢትዮጵያውያን እና ከሳምንታት በፊት ተይዘው የተፈረደባቸው 67ቱ ኢትዮጵያዊያን የዚህ የፓስፖርትና የመውጪያ ቪዛ ክልከላ ሰለባ የሆኑ ወገኖች ሲሆኑ ለእንግልታቸውና ለስቃያቸውም ግንባር ቀደም ተጠያቂውና ሃላፊው ፓስፖርትና መውጪያ ቪዛ የከለከላቸው የኢትዮጵያው ስርዓት ነው ሲሉ የሕግ ባለሙያዎች በአጽንኦት ይናገራሉ።