የአባዱላ ገመዳን የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ አገዛዙ አልቀበልም አለ

አባይ ሚዲያ ዜና
በወንድወሰን ተክሉ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ የሆኑት አባዱላ ገመዳ ለመንግስት ያስገቡት የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ተቀባይነት እንዳላገኘ ተሰማ።

የፌዴራሉ መንግስት ጠ/ሚ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ሃይለማርያም “አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ይዘት ይዘው ወደ መገናኛ ብዙሃን መሄድ አይገባቸውም ነበር” በማለት ለሪፖርተር ጋዜጣ የተናገሩ ሲሆን አያይዘውም “እኛ መደራደር ስለምንችልና ለመደራደርም ስለምንፈልግ ወደ መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን ማድረስ አልነበረባቸውም ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

አባዱላ ገመዳ በድርጅቴ ኦህዴድና በኦሮሞ ህዝብ ላይ መንግስት ክብር ስለነፈገ ከአፈጉባኤነቴ ሃላፊነት በፍቃዴ ለመልቀቅ ወስኛለሁ በማለት ደብዳቤ ካስገቡ ሁለተኛ ወሩን የያዘ ቢሆንም በመንግስት በኩል ግን እስከአሁን ድረስ መልስ እንዳልተሰጠበት ይታወቃል።

ሆኖም ከጠ/ሚ ደሳለኝ ሃይለማሪያም አገላለጽ “መንግስት መደራደር ይፈልጋል” ማለት የስራ መልቀቂያውን ሊቀበል አልፈለገም ማለት ነው ሲሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ።

የኢህአዴግ ዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነት የድርጅታችን መለያ መታወቂያ ነው ያሉት ጠ/ሚ የአቶ አባዱላ ገመዳ መውጣት ኢህአዴግን ያፈርሰዋል ብለው ለሚተቹ ወገኖች “ታላቁ መሪያችን ክብሩ አቶ መለስ ሲሞት እንኳን አልፈረስንም” ሲሉ ተናግረዋል።