ምስል ከፋይል

አባይ ሚዲያ ዜና
በወንድወሰን ተክሉ

በመቐሌ የተሰበሰበው የህወሃት አመራር አካል በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና በባለስልጣኖቻቸው ላይ መወሰድ አለበት ባሉት እርምጃ ላይ ከስምምነት ላይ መድረስ እንዳልቻሉ ከኢሳት ዘገባ ለማወቅ ተችላል።

በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው ቡድን እና አዲሱ የኦህዴድ ፖለቲካዊ አካሄድ በህወሃቶች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤና ንዴት መፍጠር እንደቻለ ከቅርብ ምንጮቻችን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን ህወሃቶች አቶ ለማ መገርሳ 《መደምሰስ አለበት》 የለም 〈መደምሰስ〉 የለበትም በሚል ሃሳብ ለሁለት መከፈላቸውንም የኢሳት ዘገባ አብራርቷል።

በህወሃትና ኦህዴድ መካከል ይፋ እየሆነ ያለው ልዩነት በመከላከያ ጄኔራሎች ጡረታ መውጯያ ውሳኔ ላይ ነው ቢባልም ታማኝ  ምጮቻችን እንደገለጹልን ከሆነ ህውሃቶች በአጠቃላይ የአቶ ለማ መገርሳን አካሄድ እንዳልተቀበሉትና በአደገኛነት እንደፈረጁት ነው መረዳት የተቻለው።

በኦሮሚያ ውስጥ ላለፉት ሁለት ዓመታት የዘለቀውን ህዝባዊውን ዓመጽ ይቆጣጠራሉ በሚል እምነት በ2016 ላይ ወደ ስልጣን እንዲመጡ የተደረጉት አቶ ለማ መገርሳ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የኢህአዴግ አስኳል ከሆነው ህወሃት ጥቅምና ፍላጎት ውጪ መጓዝ ጀምረዋል በሚል በህወሃት ባለስልጣናት ዘንድ ሲብጠለጠሉ እንደነበረ ይታወቃል።

በኦህዴድ በኩል መከላከያው መከለስ አለበት የሚል አቋም እንዲያራምዱ የጄ/ል ሳሞራ የኑስ የጡረታው ጊዜ ተጠናቆ የ5አመት ጭማሪም ተደርጎለት ካጠናቀቀም በሃላ ሌላ የአንድ ዓመት ጊዜ ታክሎለት  በመጠናቀቂያው ዋዜማ ላይ ከህወሃት በኩል ተጨማሪ አንድ ዓመት በመጠየቁ ምክንያት በኦህዴድ በኩልም ተመሳሳይ የኦሮሞ ተወላጅ ጄኔራሎች የጡረታ ጊዜ እንዲራዘም በመጠየቁ ነው ተብሏል።

ሁኔታው ከመርገብ ይልቅ እየተወጠረ በመሄዱም ምክንያት ዛሬ በመቐሌ የተሰበሰቡ ህወሃቶች በአቶ ለማ መገርሳና ግብረአበሮቻቸው መደምሰስ አለባቸው የለም መደምሰስ የለባቸውም በሚል ውዝግብ ለሁለት እንደተከፈሉ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን ህወሃቶችን ለዚህ ውሳኔ የዳረጋቸውም የአቶ ለማ መገርሳ አስተዳደር እየወሰደ ባለው እርምጃ ምክንያት እንደሆነም ለማወቅ ተችላል።

እንደ የኢሳት ዘገባ በአዛውንቱ በአቶ ስብሃት ነጋ የሚመራው አንጃ የአቶ ለማ መገርሳንና ባልደረቦቻቸውን [ቲም ለማ] በሃይል መደምሰስ አለባቸው ብሎ ሲሞግት በሌላ በኩል ደግሞ በአቶ ዓባይ ወልዱ የሚመራው ቡድን ደግሞ የለም ከእነ አቶ ለማ መገርሳ ጋር መስራት ይገባናል በማለት ክርክር እንደገጠሙ ነው መረዳት የተቻለው።

ጠ/ሚ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሐሙስ እለት ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ መንግስት የፌዴራሉ ባለስልጣን ሆነው በወንጀል ላይ በተሳተፉ ባለስልጣናት ላይ እርምጃ ይወስዳል ያሉ ሲሆን አሁንም የታሰሩ ባለስልጣናት መኖራቸውን ገልጸው በቀጣይ ቀናትና ሳምንታት ውስጥ ደግሞ በተቀሩት ላይ ይወሰዳል በማለት የመንግስትን ፍላጎት ገልጸዋል።

በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ላለፉት ወራት በተለይም በምስራቅ ኦሮሚያ ከተከሰተው ጭፍጨፋና መፈናቅል በሃላ ለህወሃቶች ያልተዋጣ ለየት ያለ እርምጃ እየወሰዱ ያሉ አመራር ሲሆን በተለይም ከጎረቤታቸው የአማራ ክልል ጋር ያደረጉት የሕዝብ ለህዝብ ስራ፣ በኦሮሚያ ውስጥ በሚካሄዱ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ፖሊስም ሆነ መከላከያው እርምጃ እንዳይወስድ ማገዳቸውና ብሎም በኦሮሚያ ውስጥ በድብቅ እርምጃ እየወሰዱ ባሉት የህወሃት ኤጀንቶች ላይ እየወስዱ ባለው እርምጃ ከህዝብ ከፍተኛ ተቀባይነትን ሲያስገኝላቸው በአንጻሩም በአገዛዙ ዘንድ ጥርስ እንዳስነከሰባቸው ለማወቅ ተችላል።

የኢህአዴግ አስኳል የሆነው ህወሃት እራሱ ከተዘፈቀበት ውስጣዊ መከፋፈልና መብላላት ሳይላቀቅ በኦህዴድ በኩል ለህልውናው የሚያሰጋ እንቅስቃሴ በማየቱ በአዛውንቱ አቶ ስብሃት ነጋ የሚመረው ቡድን አቶ ለማ መገርሳን በአቶ ድሪባ ኩማ ለመተካት ሲወስኑ በመከላከያ ውስጥ ያሉት የኦሮሞ ጄኔራሎች ለአቶ ድሪባ ኩማ ማስጠንቀቂያ በመስጠታቸው ሊሳካ እንዳልተቻለ ለማወቅ ተችላል።

የህወሃትን የጥፋት ተንኮልና እርምጃ የተረዱት አቶ ለማ መገርሳና የኦህዴድ ባለስልጣናት ድርጅታቸውን እና ሕገ-መንግስታዊ ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ እርምጃ እንደሚወስዱ የሚጠበቅ ሲሆን የሁለቱም ሃይሎች ውስጣዊ ፍጭትን በአሸናፊነት ለመወጣት ሁለቱም ወገኖች ድጋፍ በማሰበባሰብ ላይ እንዳተኮሩም ማወቅ ተችላል።