የራሺያው ፑቲን እና ዶናልድ ትራምፕ በሶሪያ ጉዳይ ተስማሙ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የራሺያው ፕሬዚዳንት ቮላድሚር ፑቲን እና የአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ በቭትናም(Vietnam) ግንኙነታቸው ወቅት በሶሪያ ጉዳይ የሃይል እርምጃ መፍትሄ እንዳልሆነ መስማማታቸውን የዛሬይቱ ራሺያ የዜና ጣቢያ ዘገበ።
ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች ዛሬ በተጀመረው የኤሺያ-ፓሲፊክ ኢኮኖሚ ትብብር ፎረም [Asia-Pacific Economic Cooperation ](APEC) ላይ ለመገኘት ከትናንት ጀምሮ በአዘጋጇ ቭትናም የተገኙ ሲሆን ከዛው ግንኙነታቸው በፊት ትናንት በተካሄደው የእራት ግብዣ ላይ አይገናኙም የተባሉት መሪዎች አብረው እንደነበሩ ተዘግቧል።

ከቀናት በፊት ሞስኮና ዋሽንግተን በሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በቭትናም የመገናኘት ሁኔታ ላይ እርሰበርሱ የሚቃረን መግለጫ በመስጠት መገናኛ ብዙሃኑን ግራ ሲያጋቡ የተስተዋለ ሲሆን በዋይት ሀውስ በኩል የሁለቱ ፕሬዚዳንቶች አንድ ለአንድ መገናኘት አለመቻል ብቻ ሳይሆን የመገናኘቱንም አላስፈላጊነትን በመግለጽ ሲጠመዱ በክሬምሊን በኩል ደግሞ በተቃራኒው የመገናኘታቸውን ፕሮግራም በመግለጽ ሲቃረኑ ተስተውለው ነበር።
በዛሬው ግንኙነታቸውም ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በሶሪያ ጉዳይ ላይ ስምምነት ላይ በመድረስ የጋራ መግለጫ እንዳወጡ ተወስቶ በዚህም ምክንያት የሶሪያ ሉዓላዊነትና ድንበር የተከበረ መሆኑን ቀሪውን ፖለቲካዊ ችግር ከወታደራዊ እርምጃ ውጪ በዲፕሎማሲና በውይይት መፈታት አለበት ሲሉ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዲሞክራቶችና አንዳንድ አክቲቪስቶች በፕሬዚዳንት ፑቲን ተረድተው ነው የ2016ቱን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉት የሚል ክስ ከከፈቱባቸውና ሴኔቱም በቀድሞ ኤፍ ቢ አይ ዳይሬክተር ሙለር የሚመራ አጣሪ ኮሚሽን ከመሰረተ በኋላ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከራሺያ ጋር የነበረውን የጨፈገገ ግንኙነት ለማሻሻል ያላቸውን ፍላጎትና ምኞት እንዳጨናገፈባቸው ይታወቃል።

ከቀዝቃዛው ጦርነት ፍጻሜ በኋላ የአሜሪካና ራሺያ ግንኙነት በዚህ ደረጃ ቀዝቅዞና ቆርፍዶ አያውቅም እየተባለ ባለበትና አሜሪካ በማእቅብ ላይ ማእቀብን እየደራረበች በመጣል ግንኙነቱን ይበልጥ ባጦዘችበት ሁኔታ የሁለቱ መሪዎች ግላዊ ግንኙነትም በተመሳሳይ መልኩ ቀዝቃዛ ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም በትናትናውና በዛሬው ግንኙነታቸው ወቅት የታየው የሁለቱ መሪዎች የእርሰበርስ መሳሳብ ኬሚካል መሪዎቹ ሳይፈልጉ በግድ በህግ መወስኛ ክፍሉ እንዲራራቁ መደረጋቸውን መረዳት ይቻላል ሲሉ ተመልካቾች ተናግረዋል።