ለዓውደ ጥናት የቀረበለትን ግብዣ በስልጣን ላይ ያለው ኢህአዴግ ሳይቀበል ቀረ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ድንበሩ ደግነቱ

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቭል ማህበረሰብ ተወካዮች እና ጋዜጠኞች ተሳታፊ የነበሩበት፣ በቪዥን ኢትዮጵያ ፎር ዴሞክራሲ በተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ሀገር በቀል ድርጅት የተዘጋጀ የአንድ ቀን ዓውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተካሄደ።

የአገራቸው ጉዳይ የጨነቃቸውና የጠበባቸው፣ ለሀገሪቱ ራዕይ ያላቸው ምሁራን ተሰባስበው የመሠረቱት ይኸው ድርጅት፣ ኢትዮጵያ ከፊትዋ የተደቀነውን መዓት ልትጋፈጥበት የምትችለውን መላ ለመምታት ባዘጋጀው መድረክ ላይ የተጋበዘው ኢህአዴግ፣ ግብዣው ቁብም ሳይሰጠው በንቀት አልፎታል።

ይህ ዓውደ ጥናት “የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባርና ሚና በዲሞክራሲ ኅብረተሰብ ግንባታ” በሚል ርዕስ በዶር ተስፋዬ ሞላ በቀረበው ወረቀት ላይ ውይይት ሲያደርግ ውሏል።

ዓውደ ጥናቱን በተመለከተ አሥተያየታቸውን የተጠየቁት የመኢአድ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ወረቀት አቅራቢውን አመሥግነው “… ሌሎችም ከአገራችን ጠላቶች ወይም ከአምባገነኖች ጋር ቆመው ከሚያጨበጭቡ እንደዚህ ትርጉም ያለው ጠቃሚ ሥራ እንዲሠሩ…” በማለት በሥም ያልጠቀሱዋቸውን ወገኖች ኮንነዋል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶር ነጋሦ ጊዳዳ አጋጣሚውን በመጠቀም ለአጠቃላይ መብት መከበር አብረን መሥራት ላይ ማተኮር እንዳለብን አበክረው አሳስበዋል።

ኢህአደግ ከገባበት አጣብቂኝ እንዲወጣ እንዴት ተመሳሳይ መድርኮችን ለራሱ ጥቅም ለማዋል አይጥርም? ተብለው የተጠየቁ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ምሁር “ዓውደ ጥናት እኮ የምሁር ነው። ያልተማረ ባለሥልጣን ዕውቀትን ይፈራል። ከቅንጅት ጋር ለመወያየት መድረክ ላይ ወጥተው የቀለሉትን እንኩዋን እነሱ እኔም አልረሳው። በዛ ላይ ደግሞ ገና ሙሉ ለሙሉ ያልመዘዙት እስካሁን ብቅ ጥልቅ የሚያደርጉት አጠቃቀሙን የረቀቁበት ካርድ አላቸው። በተለይ የህወሀትን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ሕዝቡ ነቅቶ መጠበቅ ነው ያለበት። ”በማለት ሥጋታቸውን ገልፀዋል።