የግብጽ ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያን “ሞት ወይም ሽረት” በማለት ዳግም አስጠነቀቁ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በአባይ ላይ የሚገነባው የሃይል ማመንጫ ግድብ ወደ ማጠቃላያ ደረጃ ላይ ደርሷል እየተባለ በሚነገርበት ወቅት ግብጽ ቅራኔዋን እየደጋገመች ማሰማት ተያይዘዋለች።

የግብጽ ፕሬዝዳንት የሆኑት ኤል ሲሲ በአባይ ወንዝ እና በሚገነባው የሃይል ማመንጫን አስመልክቶ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያን ለማስፈራራት ሲሞክሩ መደመጣቸው ይታወሳል።

በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብ የግብጽን ህልውና በምንም አይነት ሂሳብ አደጋ ላይ የማይጥል እንደሆነ ከኢትዮጵያ በኩል በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል።

የሃይል ማመንጫው በሚገነባበት በአባይ ወንዝ የሚደረገውን የገለልተኛ ቡድን ጥናት እንደማይቀበሉ ሱዳንና ግብጽ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ይህንን ገለልተኛ የሆነ የ3ኛ ወገን ጥናት ሱዳንና ግብጽ እንደማይስማሙበት ማሳወቃቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ሲሲ ዳግመኛ ኢትዮጵያ ላያ ዛቻቸውን መሰንዘራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

ፕሬዝዳንት ኤል ሲሲ በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ በማለት “ውሃ የሞትና የህይወት ሽረት እንደሆነ” አጽንኦት በመስጠት ለግብጻውያን ንግግር ማድረጋቸውም ተዘግቧል።

“ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን የውሃ ድርሻ ማንም ሊነካ አይችልም” በማለት ፕሬዝዳንቱ በዚሁ የቴሌቭዥን ንግግራቸው ግብጻውያንን ለማሳመን ሲጥሩ ተደምጠዋል።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን የመጠቀም መብት እንዳላትና ይሄንንም ለማድረግ ማንንም ፍቃድ የመጠየቅ ግዴታ እንደሌለባት መግለጿ ይታወሳል።

በአባይ ወንዝ  ላይ የሚገነባው የሃይል ማመንጫ በሱዳንም ሆነ በግብጽ የውሃ አቅርቦት ላይ እንደሚጋነነው አይነት ተጽእኖ እንደማያመጣ ኢትዮጵያ እንዳረጋገጠች ሲዘገብም ቆይቷል።