የዚምብዋቡዌ ሕዝብ ሙጋቤ ከስልጣን ይውረዱ ሲል ሰልፍ ወጣ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
በወንድወሰን ተክሉ

ዚምቡዋቡዌያዊያን በሀገሪቱ ዋና ከተማ ሀራሬና በሁለተኛዋ ከተማ ቡላሃዋዬ ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ስልጣናቸውን እንዲለቁ መጠየቃቸውን ቪ.ኦ.ኤ ዘገበ።

በሀራሬ ዚምቡዋቡዌ አደባባይ የተገኙት ሰልፈኞች ቁጥር በአስር ሺህ እንደሚቆጠር የተገለጸ ሲሆን በጋለ ስሜት ሙጋቤ ከስልጣን ይውረዱ እያሉ ሲጠይቁ እንደዋሉ ተዘግቧል።

የ93ዓመቱ አዛውንት ፕሬዚዳንት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ ሀገሪቷን ላለፉት 37ዓመታት የመሩ ሲሆን ከባለፈው ረቡእ ጀምሮ በጦር ሰራዊቱ እርምጃ ከስልጣናቸው ወርደው በቁም እስር እንዳሉ ይታወቃል።

በጄ/ል ኮንስታንቲን ቹዌንጋ የሚመራው ጦር ሃይል ፕሬዚዳንቱን ከስልጣን ያወረዳቸው ጦር ኃይል እስከ ዓርብ እለት ከስልጣን መልቀቃቸውን እንዲገልጹ ቀነ-ገደብ የሰጣቸው  ቢሆንም እሳቸው ግን ፍቃደኛ ባለመሆን ስልጣኔን አለቅም በሚል አቋም እንደጸኑ ተዘግቧል።

ቅዳሜ በተካሄደው ሀገር አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተሳተፈው ህዝብ “የሰራዊቱ እርምጃ መፈንቅለ መንግስት አይደለም፣ ሙጋቤ ከስልጣን ይውረዱ” እና መሰል መፈክሮችን ሲያሰማ እንደዋለ የተገለጸ ሲሆን የጄ/ል ኮንስታንቲን ቺዌንጋን ፎቶ የያዙ ሰልፈኞችም ታይተዋል።

በዚምቡዋቡዌ ታሪክ በተለምዶ ሰላማዊ ሰልፈኞችን በመበትን ተግባሩ የሚታወቀው ሰራዊት በቅዳሜው ሰላማዊ ሰልፍ ግን ሰልፈኛው ወደ ቤተመንግስት እንዳይጓዝ መንገድ በመዝጋት ከሰልፈኞቹ ጋር ተቀላቅሎ ተቃውሞውን በማስተጋባት ደረጃ ሲሳተፍ መታየቱ ተዘግቧል።

የሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያና ዘ-ሔራልድ የተባለ ጋዜጣም ባልተለመደ መልኩ ሰፊ ሽፋን በመስጠት የሰልፈኛውን ጥያቄ ሲያስተጋቡ መዋላቸው ተገልጿል።

ፕሬዚዳንቱን ከስልጣን ያወረደውና በቁም እስር ስር ያዋለው ጦር ኃይል ለፕሬዚዳንቱ በሰላማዊ መንገድ ከስልጣን እንዲለቁ የሰጠቻው ቀነ ገደብ ዓርብ እለት በመጠናቀቁ ሀገር አቀፍ ተቃውሞ ሰልፍ እንዲካሄድ መፍቀዱና ማስተባበሩም መገናኛ ብዙሃን እየገለጹ ይገኛሉ።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ የደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት ልማት ማህበር ሊቀ መንበርነታቸው በመጠቀም በዚምቡዋቡዌ ጉዳይ ላይ የሚመክር አስቸካይ የመሪዎች ስብስባ በቦትስዋና እንዲካሄድ ጥሪ ማድረጋቸውም ተገልጿል።

ፕሬዚዳንት ሙጋቤ በቁም እስር ላይ ሆነው ካሰራቸው ጦር መሪዎች ጋር እየተደራደሩ እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን ከስልጣን ሊነሱ የቻሉት ም/ል ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምዋንጋጉዋን ከስልጣን በማባረራቸው ምክንያት እንደሆነ የጦር ሰራዊቱ ቃል አቀባይ ገልጸዋል።

በመጪው ዓመት የስልጣን ዘመናቸው የሚያበቃው ሙጋቤ አሁን ስልጣኔን የምለቅበት ሰዓት አይደለም በማለት የጦሩን፣ የገዢውን ፓርቲና የህዝቡን ጥያቄ አልቀበልም እንዳሉ ነው።

ፕሬዚዳቱን ከስልጣን ያወረደው ጦር ሃይልም በተባረሩት ም/ል ፕሬዚዳንት ምትክ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ባለቤታቸውን ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤን ለመተካት አስበዋል በማለት ሲሆን፤ የተባረሩት ም/ል ፕሬዚዳንት ኤመርሰን የነጻነት ታጋይ የነበሩ፣ በገዢው ፓርቲና በጦር ሃይሉ የተወደዱና ፕሬዚዳንቱንም ይተካሉ ተብለው የተጠበቁ የ75 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ተመራጭ እጩ እንደነበሩ መነገሩ ይታወሳል።