አቶ በረከት ግጭቶቹ የተፈጠሩት በነባሩና አዲሱ አመራር ነው ማለታቸው ተሰማ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
አክሊሉ ታደሰ

ህወሀትና ብአዴን ጎንደር ላይ ባዘጋጁት ኮንፍረንስ ላይ የተገኙት አቶ በረከት ሲሞን በመላው ኢትዮጵያ የሚታዩት ግጭቶች ሰፍተው አዲስ አበባ ጫፍ ላይ መታየት የተለመደ ሆኗል ሲሉ ግጭቶቹም ነባሩና አዲሱ አመራር የፈጠረው ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

አቶ በረከት በጎንደር ከተማ በተደረገውና በህወሀትና ባዴን የጋራ ኮንፍረንስ ላይ ተገኝተው በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ስርአት ለኢትዮጵያ ልማት ሰላምና ዲሞክራሲ በሚል ርእስ ባደረጉት ንግግር የትኛውም የኢትዮጵያ ብሄር ሌላ ብሄር ነው የሚያስተዳድረኝ ሊል አይችልም ሁሉም ራሱን በራሱ ነው የሚያስተዳድረው ማለታቸውና ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ማእከል በማድረግ የተገነባው ፌደራሊዝም አንዱ ሌላውን በማስተዳደር ይጫነዋል እንዳይባል ተደርጎ የተቀየሰ ነው በማለት ስርአቱ ችግር እንደሌለበት ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

አቶ በረከት በዚሁ ጨምረውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገሪቱ ውስጥ በስፋት የሚታዩት ግጭቶች ነባሩና አዲሱ አመራር የፈጠሩት እንጂ የብሄራዊ ደህንነት ም/ቤት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ እንዳለው የውጭ ሀይሎች ያለመሆናቸውን ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

ጠንካራ ተቃውሞ እየቀረበበትና በቀዝቃዛው ተጀምሮ በቀዝቃዛው የተጠናቀቀው የህወህትና ብአዴን ኮንፍረንስ ከፍተኛ ጥበቃና ፍተሻ ይደረግበት እንደነበረና ተሳታፊ የተባሉትም የኮንፍረንሱ ታዳሚዎች አዳራሹን ከመሙላት ያለፈ የተወራለትን ውጤት ማስገኘት የሚችሉ አልነበሩም ሲሉ ብዙ ታዛቢዎች በተለያየ መንገድ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ተስተውሏል፡፡