አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

ከፓርቲ ሊቀመንበርነት ስልጣናቸው እንዲነሱ የተደረጉት ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ በቀጥታ በተላለፈ የቴሌቭዝን ስርጭት ከፕሬዝዳንትነታቸው እንደማይለቁ ተናገሩ።

ለአመታት ሲመሩት የነበረው ፓርቲያቸው ዛኑ ፒኤፍ በ24 ሰአታት ውስጥ የፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸውን እንዲለቁ መወሰኑም ይታወሳል።

የፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸውን እንዲለቁ ከፓርቲያቸው በተጨማሪም ህዝቡ ግፊት እያደረገባቸው የሚገኙት ሮበርት ሙጋቤ በስልጣነ መንበራቸው ለ አንድ ወር ያህል እንደሚቆዩ አሳውቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ በስልጣን እቆያለው ይበሉ እንጂ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ያለፍቃዳቸው ከፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸው ሊወገዱ እንደሚችሉ የፖለቲካ ተንታኞች በአለም አቀፍ የሚዲያ አውታሮች ላይ እየተናገሩ ይገኛሉ።

ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ንግግራቸውን ያሰፈሩባቸው ብዛት ያላቸው ወረቀቶችን ለመለየት ሲቸገሩ  እና በቦታው የነበሩት የጦር ሹሞች እነዚህን ወረቀቶች ለፕሬዝዳንቱ ሲያስተካክሉ በቀጥታ በተሰራጨው የቴሌቭዥን ፕሮግራሙ ለማስተዋል ተችሏል።

ሮበርት ሙጋቤ በፍቃደኝነት ፕሬዝዳንትነታቸውን እንደማይለቁና በግድ እንዲለቁ መደረግ እንዳለበት ከፕሬዝዳንቱ የቀጥታ የቴሌቭዥን ንግግር በሃላ አስተያየታቸውን የሚሰጡ የዛኑ ዴፍ ፓርቲ አባላት ተገኝተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ስልጣናቸውን  ከአንድ ወር በፊት ላለማስረከብ እንዲህ ሙጥኝ ያሉት ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ደህንነት ማረጋገጫ የሚያገኙበትን ጊዜ ለመግዛት እንደሆነም የዙምባቤ ምሁሮች ትንታኔያቸውን ይሰጣሉ።