አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በፈረንሳይ ከዋናዋ ከተማ ፓሪስ በስተሰሜን በምትገኝ ከተማ አንድ የፖሊስ ሰራዊት ሶስት ሰዎችን ገድሎ እራሱን ማጥፋቱ ተዘገበ።

የፖሊስ ሰራዊቱ የ31 አመት ጎልማሳ እንደነበረና ሰዎቹን ለመግደል የተጠቀመበት መሳሪያም የእለት ስራውን እንዲያከናውንበት የተሰጠው መሆኑን ተዘግቧል።

ፖሊሱ ይህንን የግድያ ድርጊት የፈጸመበት ምክንያት የቤተሰብ ግጭት ሳይሆን እንደማይቀር በክስተቱ የተጎዱት ሰዎችን በማመሳከር እየተገለጸ ይገኛል።

ከሟቾቹ አንዱ ግለሰብ የገዳዩ የሴት ጋደኛ ወይም ፍቅረኛ አባት ሲሆኑ የተቀሩት ሁለቱ ግለሰቦች ግን መንገድ አላፊዎች እንደነበሩ የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ግድያውን የፈጸመው የፖሊስ ሰራዊት ፍቅረኛውን በመኪና ውስጥ እንደተቀመጠች ፊቷ ላይ ተኩሶ እንዳቆሰላት ተገልጿል።

ይህ ፖሊስ ይህን ግድያ ከመፈጸሙ በፊት ለተከታታይ ጊዜያት የፍቅር ግንኙነታቸው መቋረጡን ስትገልጽለት እንደነበር እየተነገረም ይገኛል።

የፍቅረኛውንም እናትና እህት በያዘው መሳሪያ ተኩሶ እንዳቆሰላቸው በተጨማሪ ከሚወጡ መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል።

ይህ የፖሊስ አባልና ለሶስት ሰዎች ህይወት መጥፋት መንስኤ የሆነው ግለሰብ በስተመጨረሻ የገዛ ነፍሱን በያዘው መሳሪያ እንዳጠፋ ተዘግቧል።