ማኅበረ ቅዱሳን በውጭ ለሚኖሩ ታዳጊዎች ማስተማርያ ሥርዓተ ትምህርት አዘጋጅቶ አስመረቀ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቢሰሎም ፍሰሃ

በያዝነው ወር ህዳር 3, 2010 ዓም እንግሊዝ ዋና ከተማ ለንደን ከተማ በምትገኘው ደብረ ገነት ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን የተመረቀው የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅቱ ከሁለት ዓመት በላይ ወስዷል። ዝግጅቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ ከሶስት መቶ በላይ የሚሆኑ በእንግሊዝ የሚኖሩ ምእመና እና ከሰላሳ ያላነሱ የቤተ ክርስቲያን ወጣት ምሁራን ተሳትፈውበታል።

ጥናቱ የአብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ፣የልጆች የቋንቋ ክህሎት እና የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ደረጃ፣ እንደዚሁም ወላጆች የተሳተፉበት በችግሮች እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ዙሪያ ያተኮረ የመነሻ ጥናት ተደርጎበታል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አንዱ እና ፈታኙ ጉዳይ ልጆቻቸውን በሚፈልጉት ሃይማኖት እና ኢትዮጵያዊ ባህል አሳድጎ ለቁምነገር ማብቃት ነው። ችግሩን ለመፍታት በባለሙያ የተዘጋጁ ልጆችን የማስተማርያ በቂ ስርዓተ ትምህርት አለመኖር ተጠቃሽ ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ ስር የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማዕከል ስር የሚገኘው የተተኪ ትውልድ ሥልጠና ክፍል ይህንን ችግር ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

በስርዓተ ትምህርቱ ምረቃ ላይ ከእዚህ በፊት ሕፃናትን እንዴት እናስተምራቸው በሚል ርዕስ መፅሐፍ ያሳተሙት የዚህ ስርዓተ ትምህርት ዝግጅት አስተባባሪ እና የማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማዕከል ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ጨከነ በላቸው የሥርዓተ ትምህርቱ ዝግጅት ላይ አስተዋፅኦ ያደረጉ ከሰላሳ በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምሁራን ወጣቶች መሳተፋቸውን ገልፀዋል።

ከአምስት እስከ ዘጠኝ ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሕፃናትና ታዳጊዎች ታስቦ የተዘጋጀው ይህ ሥርዓተ ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ የአማርኛ ቋንቋ እና የመዝሙር ጥናት የተሰኙ አምስት የትምህርት ዘርፎችን ያካተተ ሲኾን፣ የትምህርቶቹ አርእስትና ይዘቶችም በቤተ ክርስቲያን የሚከበሩ በዓላትንና ወቅቶችን መሠረት በማድረግ የተዘጋጁ ናቸው፡፡