የዚንባቡዌውን መሪ የሚተኩት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ትናንት ሐረሬ ገቡ ቃለ መሃላም ነገ ዓርብ እንደሚፈጽሙ ተገለጸ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ብርሃኑ አየለ

ከሁለት ሳምንታት በፊት  በፕሬዚደንት ሙጋቤ ተባረው በደቡብ አፍሪካ ተደብቀው ከቆዩ በኋላ ገዥው ፓርቲና የሃገሪቱ ጦር ኃይል በመተባበር ፕሬዚደንት ሙጋቤን ከሥልጣን በማዉረድ ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩት ኤመርሰን ምናንጋግዋ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ በጊዜያዊነት ፕሬዚደንት ሙጋቤን በመተካት ፕሬዚደንት እንዲሆኑ በተደረሰበት ስምምነት መሰረት ይህንን ሃላፊነት ለመሸከም በትናንትናዉ እለት ዚምባቤዌ መግባታቸዉን ሲኤንኤን (CNN) ዘገበ።

ይኧው የዜና ምንጭ በነገው ዕለት ቃለ መሃላም እንደሚፈጽሙ ገልጿል። አዞዉ(Crocodile) በመባል የሚታወቁት ኤመርሰን የነጩን አናሳ አገዛዝ ለመጣል በተደረገዉም ትግል ከአሉት ነባር ታጋዮች ዉስጥ ከዋናዎቹ አንዱ ሲሆኑ በፖለቲካ ብልጠታቸዉና በትግል ጥንካሬአቸው አንቱ የተባሉ ሰው እንደነበሩ በብዙ ምንጮች እየተነገረ ነዉ።

በሚቀጥለው መስከረም 2018 በሚካሄደዉ ምርጫ ዉሳኔአቸዉ ምን እንደሆነ በግልፅ ባይናገሩም የምረጡኝ ዓይነት ቅስቀሳ በሚመስል መልክ ዛሬ የምንመሰክረዉ ”ታፍኖ የነበረው ዲሞክራሲ መለቀቁን“፤“የሕዝብ ድምፅ የአምላክ ድምፅ መሆኑን ነዉ” ፤ “ለዚቺ ለደሀ አገር ብልፅግናና መረጋጋትን አመጣለሁ፤”“የእናንተ አገልጋይ ለመሆን ቃል እገባለሁ።” የሚሉ ተስፋዎችን ለደጋፊዎቻቸዉ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ፕሬዚደንት ሙጋቤ ሥልጣናቸዉን በመልቀቃቸዉ ሕዝብ ደስታዉን በአደባባይ ቢገልጽም ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ ኤመርሰን የፕሬዚደንት ሙጋቤ የቀኝ እጅ በመሆን አብረው ለረጅም ጊዜ የቆዩ በመሆናቸው ከፕሬዚዳንት ሙጋቤ ባልተናነሰም በብዙዎች እንደሚፈሩም ተገልጿል። ምንም እንኳን ኤመርሰን በእልቂቱ የእርሳቸው እጅ እንዳልነበረበት ገልፀው  የነበረ ቢሆንም  በ1980  በሰሜን ኮርያ በሰለጠኑት የአምስተኛ ብርጌድ አማካይነት በፖለቲካ ተቀናቃኛችና ዜጎች ላይ  ዕልቂት በተፈፀመበት  ወቅት የነበረው የስለላ መረብ ሹም እንደነበሩ ይታወቃል።

ያም ሆነ ይህ ሁሉም ነገር ወደፊት የሚታይ ሲሆን ብዙ ታዛቢዎች በሦስተኛው ዓለም ባልተለመደ መልኩ አገሪቱ ያፈራቻቸው ሀብቶች ሳይወድሙና ከሁሉም በላይ ክቡር  የሆነው የዜጎች ሕይዎት ሳይጠፋ እንደዚህ ያለ ሽግግር እሰየው የሚያስብል ነው በማለት ለሌሎችም ያለዉን ምሳሌነት ትኩረት በመስጠት በአወንታዊ ገጽታው ተመልክተዉታል።