የተሰወረውን የጋንታ ሀይል ፍለጋ የወጡ ወታደሮችም እንደ ወጡ መቅረታቸው ተሰማ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
አክሊሉ ታደሰ

በደቡብ ኢትዮጰያ ሞያሌ አካባቢ ከሰፈረው የ10ኛ ክ/ጦር አካል የሆነውና በአንድ የሀይል አዛዥ የሚመራ ከ30 በላይ ወታደሮችን የያዘው የጋንታ ሀይል ለአሰሳ ወጥቶ መቅረቱን ተከትሎ ለፍለጋ ከተሰማሩት የክ/ጦሩ ወታደሮች ውስጥ ሳይመለሱ የቀሩ ወታደሮች እንደሚገኙ ተሰማ፡፡

ኢሳት እንደዘገበው ከኣራት ቀን በፊት ለአሰሳ ወጥቶ በዚያው የተሰወረውን የጋንታ ሀይል ፍለጋ ቦረና፤ ዋቤሎን ይዞ እስከ ኬንያ ድንበር ድረስ የተንቀሳቀሰው የፍለጋ ቡድን የተሰወሩትን ወታደሮች ከማግኘት ይልቅ ለፍለጋ ከወጡት ወታደሮች ውስጥ በቡድንና በተናጠል እየኮበለሉ መሆኑ ታውቋል፡፡የወታደሮቹ መኮብለል ከተሰማበት እለት ጀምሮ በ10ኛ ክ/ጦር ውስጥ በሚገኙ በተለይም የአማራና ኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ወታደሮች ላይ ልዩ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑም ታውቋል፡፡

መንስኤው በውል ባልታወቀ ሁኔታ ከነሙሉ ትጥቁ በተሰወረው የጋንታ ሀይል ምክንያት የ10 አለቃ ረጋሳ የተባለ የሬዲዮ መገናኛ ሰራተኛ የተሳሳት መረጃ በማቅረብ በሚል ለእስር የተዳረገ መሆኑን ጨምሮ በሁለት መስመር ለፍለጋ የተሰማራው አሳሽ ሀይል እስከአሁን ድረስ ወደ ካንፑ ያልተመለሰ ይልቁንም ተጨማሪ ራሽን የተላከለት መሆኑንም በዝርዝር ተዘግቧል፡፡

በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በብዛት የሚከዳውን የሰራዊት አባላት በተመለከተና በምትኩ የተፈለገውን ያህል የሚመለመል የሰው ሀይል ማግኘት ያለመቻሉ ለስርአቱ የጦር ሹማምንት የራስ ምታት ሆኖ የከረም ጉዳይ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲዘገብ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡