ወ/ሮ አዜብ ይቅርታቸውን ከነምክንያታቸው ለድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ በደብዳቤ እንዲያቀርቡ ተገደዱ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በመቀሌ የሚደረገው የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት) እርስ በእርስ ግምገማና የድርጅቱ ውስጣዊ ፍተሻ እንደቀጠለ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከዚህ ቀደም ይህን ስብሰባ ረግጠው የወጡት የሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር የአቶ መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ  አዜብ መስፍን በዚህ ስብሰባ እየተሳታፉ እንደሆነም ተጠቁሟል።

ወ/ሮ  አዜብ መስፍን ዳግም ድርጅቱ በሚያደርገው ጥልቅ የግል እና የድርጅት ግምገማ ላይ እንዳይሳተፉ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገልጹ የነበሩ አባላት እንደነበሩም እየተነገረ ይገኛል።

ድርጅቱ ከዚህ በፊት ሲያደርግ የነበረውን ስብሰባ ረግጠው በመውጣት ባለቤታቸው አቶ መለስ ዜናዊ የተጋደሉለትንና እስከ እለተ ሞታቸው ሲመሩት የቆዩትን ድርጅት በማዋረዳቸው አባላቱ በወ/ሮ  አዜብ መስፍን ላይ ከፍተኛ ቅሬታና ተቃውሞ እንደያዙም እየተወራ ነው።

ወ/ሮ  አዜብ በንቀት ስብሰባውን ረግጠው የወጡበትን ምክንያት ለማስረጃነት እንዲያገለግል በሚል እሳቤ በደብዳቤ እንዲያቀርቡ አሊያም ድርጅቱ እያደረገ ባለው ስብሰባ ላይ ዳግም እንዳይገኙ አባላቱ መወሰናቸውንም ውስጥ ለውስጥ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በዚህ ስብሰባ ላይ ዳግም ለመሳተፍ ወ/ሮ አዜብ አማላጅ በመላክ የድርጅቱን አባላት በግንባር በመገኘት ይቅርታ ቢጠይቁም የተወሰኑ የድርጅቱ አባላት ይቅርታቸውንና ስብሰባውን የረገጡበትን ምክንያት በጽሁፍ እንዲያቀርቡ ማስገደዳቸውንም ተሰምቷል።

በይዘቱ ከዚህ በፊት ድርጅቱ ካደረጋቸው ስብሰባ ጠጠር ያለ በተባለበት በዚህ የግምገማና እራስን የመፈተሽ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወ/ሮ አዜብ በቅርቡ ስብሰባ ረግጠው የወጡበትን ምክንያት ዝርዝር በደብዳቤ ጽፈው ለማእከላዊው ኮሚቴ አስገብተዋል ተብሏል።

በዚህ የህውሃት ከፍተኛ አመራሮች እርስ በእርስ በግምግማ በሚጠዛጠዙበት ስብሰባ ላይ ድርጅቱን ለዚህ ለማብቃት የተሰዉት ታጋዮችን አደራ በተግባር ከማዋል ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም እንዳስቀደሙ በግልጽ ሲወቃቀሱ እንደነበር  የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

አመራሮቹ በዚህ የሰላ ትችት ከመቀጣቀጣቸው የተነሳ  አንጃና ቡድን ፈጥረው እንደተከፋፈሉና ስብሰባውም ጠብና ውጥረት የተሞላበት እንደሆነ እየተሰማ ይገኛል።

በዚህ የህውሃት ስብሰባ ላይ አባላቱ እርስ በእርሳቸው በሙስና ብሉሽነት፣ በሃብት ምዝበራ፣ ሆን ተብሎ የተሳሳተ ሪፖርቶች በማቅረብ፣ በስልጣናቸው ያልሰሩትን እንደሰሩ እያደረጉ በማቅረብ በሚል ሂስ ጠብ ድረስ በሚደርስ ግምገማ ሲጠዛጠዙ እንደቆዩ  መረዳት ተችሏል።

ከዚህ በፊት ከህውሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት የወጡ ግለሰቦችን ዳግም ወደ ኮሜቴው ለማምጣት የተጠቀሰውን ሃሳብ ከጥቂት አባላት በስተቀር በሌሎቹ ድጋፍ ማግኘቱንም  እየተሰማ ነው።

የመቀሌ ከተማም ለዚህ ስብሰባ ከወትሮ ይልቅ በከፍተኛ የጸጥታ ሃይሎች እየተጠበቀች እንደሆነና የማእከላዊው ኮሚቴ አባላቱ በግምገማው ገበና መወጣጣት እንደተያያዙ የቀድሞ የህውሃት ማእከላዊ አባል የነበሩት አቶ አሰገደ ገብረ ስላሴ እየተናገሩ ይገኛሉ።

የድርጅቱ ወቅታዊ ከፍተኛ አመራሮች ከቀድሞ አመራሮች ጋር በዚህ ስብሰባ የሚያደርጉት የእርስ በእርስ ዘለፋና ግምገማ እንደሚቀጥልም ተሰምቷል።