ዳኛ ዘርዓይ ፍርድ ቤት ውስጥ ተከሳሾችን ምንም አታመጡም ማለታቸው ታወቀ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ናትናኤል ኃይለማርያም

በተሻገር ወልደሚካኤል የክስ መዝገብ ጉዳያቸዉ ሲታይ የነበሩት ተከሳሾች በዳኛ ዘርዓይ በደል እንደደረሰባቸው እና ተከሳሾቹም በአንድ ድምጽ ተቃውሞ ማሰማታቸው ታውቋል።

ዳኛ ዘርዓይ እና አብረውት የተሰየሙት ዳኞች የተከሳሾቹን ቃል ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከተከሳሾቹ አንዱ የሆነው አቶ አስቻለው የለበሰውን ሱሪ በማውለቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደኝ በማለት እስር ቤት በነበረበት ጊዜ በሕወሐት ጨቃኝ ገራፊዎች ብልቱ መቀጥቀጡን በችሎት ውስጥ ለነበሩት ሁሉ አሳይቷል።

ይህ ጭካኔ የተሞላበት ሰቆቃ በችሎቱ የተሰበሰቡትን ሁሉ ያስለቀሰ እና በጣም ያሳዘነም እንደነበር ሲዘገብ ዳኛ ዘርዓይ ምን ታመጣላችሁ ማለቱ ችሎት ለመከታተል የመጣውን ሕዝብ ክፉኛ እንዳስቆጣ ታውቋል።

ዳኛ ዘርዓይ ይባስ ብሎም አቤቱታ የሚያቀርበውን ተከሳሽ ሲያቋርጠው ከተከሳሾች አንዱ ሃሳቡን ይጨርስ ብሎ በመናገሩ ወደ ችሎቱ እንዲቀርብ አድርጓል።

ተከሳሾቹም ምንም አይነት ወንጀል እንዳልሰሩ በመግለጽ ወንጀል ሆኖ ይህን ሁሉ መከራ የሚያስከፍለን አማራ መሆናችን ብቻ ነው ሲሉ መደመጣቸውም ታውቋል።

የልደታ ፍርድ ቤት ከዚህ ጋር በተያያዘ በነተሻገር ወልደሚካኤል ክስ መዝገብ በተከሰሱት እነዚህ ተከሳሾች ላይ በቀጣዩ ቀን በዋለው ችሎት ችሎት በመድፈር ሲል 1ኛ ተከሳሽ ተሻገር ወልደሚካኤልን የ3 ወር እስራት ሲቀጣ 7ኛ ተከሳሽን አቶ በለጠ አዱኛን 8ኛ ተከሳሽ አቶ ተስፋሚካኤል አበበን እና 9ኛ ተከሳሽ የሆነውን አቶ እንዳለው ፈቃዴን እያንዳንዳቸውን 6 ወር መፍረዱም ታውቋል።

ተከሳሾቹም ወንጀል ሰርታችኋል በተባልንበት ቦታ ጉዳያችን ሊታይ ይገባል ብለው ያቀረቡትን አቤቱታ ዳኞቹ አቤቱታውን ለመስማትም ሆነ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ተከሳሾቹ ተቃውሟቸውን ማቅረባቸው ታዉቋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ዜና፣ እነ ተሻገር ወልደሚካኤል ለታሕሳስ 11 የተቀጠሩ መሆናቸው ሲታወቅ የ4ኛ ችሎት የግራ ዳኛ የሆነው ዘርዓይ ጉዳያችንን ሊመለከት የሚያስችለው የሞራል ብቃት የለውም ሲሉ በመቃወም እንዲነሳላቸው አቤቱታ ማስገባታቸው ታዉቋል።