አባይ ሚዲያ ዜና
አክሊሉ ታደሰ

ቅዳሜ ህዳር 16 በጎንደር ከተማ ተሰብስበው ይጨፍሩ በነበሩ የፋሲልና ወልድያ ከነማ የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ላይ ተኩስ የከፈተው የመከላከያ ሰራዊት ባልታወቀ ሀይል የአጸፋ ተኩስ ተከፍቶበት ከፉኛ ጉዳት እንደደረሰበት ታወቀ፡፡

ነገ እሁድ ህዳር 17 በጎንደር ከተማ ለሚደረገው የፋሲል ከነማና የወልድያ አቻው የእግር ኳስ ግጥሚያ ወደ ጎንደር የመጣውን የወልዲያ ቡድን ለመቀበል በወጣውና እስክ ጠዳ ድረስ ተጉዞ ቡድኑን አጅቦ እየጨፈረ በመጣው የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊ ላይ ተኩስ በመከፈቱ ምክንያት በተከተለው የአጸፋ የተኩስ እሩምታ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ ታውቋል፡፡

የቡድኖቹ ደጋፊዎች ሀገራዊና ቀስቃሽ ዘፈኖች እያሰሙ ቀበሌ 17 ቄራ ከተባለ አካባቢ ሲደርሱ በ2 ወታደራዊ ተሽረርካሪዎች ላይ መትረየስና ስናይፐር የጠመዱ የመንግስት ወታደሮች በህዝብ ላይ ተኩስ በመክፈታቸው  በአካባቢው ሸምቆ የነበረና ለጊዜው ማንነቱ ያልታወቀ ሀይል የአጸፋ ተኩስ በመክፈት ጉዳት አድርሰው መሰወራቸው ተሰምቷል፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ ከአዘዞ ወታደራዊ ካምፕ ወጥቶ በቡድኑ ደጋፊዎች ላይ ተኩስ የከፈተው ቀድሞ ከስፍራው የነበረው የክልሉ ልዩ ሀይል ሁኔታውን በዝምታ በማለፉ በተበሳጩ የደህንነት ሹማምንት በተሰጠ ታእዛዝ ነው መባሉንም ዘገባው ያስረዳል፡፡

ለጊዜው ለማረጋገጥ ባይቻልም በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች ላይ ተኩስ የከፈቱት የመንግስት ወታደሮች በህዝብ ላይ የከፋ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ለመከላከል የአጸፋ ተኩስ በመክፈትና በወታደሮቹም ላይ ጉዳት ያደረሱት ሸማቂዎች የአርበኞች ግንቦት ሰባት አርበኞች ናቸው ሲሉ በስፍራው የነበሩ ሰዎች ሲናገሩ መሰማቱንም ያገኘነው መረጃ ያረጋግጣል፡፡

በዚህ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ በተሰማበት ህዝብን ከመንግስት ወታድሮች ጥቃት ለመከላከል በተባለውና በተወሰደው እርምጃ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ባይታወቅም በአካባቢው አንቡላንሶች ሲሯሯጡ መታየታቸው ታውቋል፡፡