አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በቱርክ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ የሚያገለግል ግለሰብ ሲነዳ በነበረው መኪና ሌሎች መኪኖችን በመግጨት  ጉዳት ማድረሱ ተሰማ።

ግለሰቡ ሲያሽከረክር በነበረው መኪና ያደረሰው የትራፊክ አደጋ የተከሰተው ህዳር 18 ቀን 2010 ዓም እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በግጭቱ መኪናቸው የተጎዱ ሁለት የቱርክ ዜጎች ከኤምባሲው ግለሰብ ጋር ለመነጋገር ሲሞክሩ ማስፈራሪያና ዛቻ እንደወረደባቸው ተናግረዋል።

አደጋውን ለመመርመር በቦታው የተገኙት ፖሊሶችንም ይህ የኤምባሲ ሰራተኛ በቱርክና በኢትዮጵያ መካከል ጦርነት ማስነሳት እንደሚችል በመናገር ሲያስፈራራና ሲዝት  እንደነበረ ተዘግቧል። የኤምባሲ ሰራተኛው አልኮል ጠጥቶ እንደሆነና እንዳልሆነ ምርመራ እንዲያደርግ በቱርክ ፖሊስ ጥያቄ ቢቀርብለትም አሻፈረኝ ብሏል።

ፖሊሶቹ የአልኮል መጠን ምርመራ እንዲያደርግ ውትወታቸውን ካላቆሙ በቱርክና በኢትዮጵያ መካከል የዲፕሎማቲክ ጦርነት እንደሚያስጭር ዳግም ሲዝት እንደነበረም ታውቋል።

በኢትዮጵያ ኤምባሲ ተቀጥሮ የሚያገለግለው ይህ ግለሰብ ባደረሰው ሁለት የትራፊክ አደጋዎች ምክንያት በአንካራ ፖሊሶች ላይ እንዲሁም ጉዳቱ በደረሰባቸው ግለሰቦች ላይ ሲሰነዝር የነበረውን ዛቻ እንደሰሙ በቦታው የተገኙ ሰዎች ቃላቸውን ሰጥተዋል።

የኤምባሲው ሰራተኛ አልኮል የሚባል ነገር እንዳልቀመሰ ነገር ግን ምርመራ ለማድረግ ፍቃደኛ አለመሆኑንም ሲናገር መደመጡ ተሰምቷል።