በወልዲያ ከተማ የመንግስት ሃይሎች በህዝብ ላይ ለወሰዱት እርምጃ ህዝቡ የአፀፋ እርምጃ አየወሰደ እንደሆነ ተሰማ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቢሰሎም ፍሰሃ

በመቀሌና በወልዲያ እግር ኳስ ደጋፊዎች መካከል የተነሳው ተቃውሞ ወደ ህዝባዊ አመጽ ተቀይሮ የወልዲያ ህዝብ አገዛዙን በስለላ ተግባር ይረዳሉ የሚሉትን ተቋሞችን፣  ሱቆችን እና ድርጅቶችን ማቃጠል መጀመራቸው ተሰምቷል።

የመቀሌ ከነማ ደጋፊዋችን ይዘው የመጡ ሁለት መኪኖች ጥቃት ሲደርስባቸው ደጋፊዎቹ ሆቴል ውስጥ እንዲገቡ ተደርገው ሆቴሉ በፌደራል ሰራዊት መከበቡም ተገልጿል።

የፋሲል ከነማ ቡድን ውድድር ሊያደርግ ወደ መቀሌ ተጉዞ በነበረበት ወቅት የቡድኑ ደጋፊዎች በመቀሌ ከተማ የድብደባ ጥቃት ሲደርስባቸው ምንም አይነት ከለላና ጥበቃ እንዳልተደረገላቸው በመግለጽ በወልዲያ በሆቴል ውስጥ የተጠለሉትን የመቀሌ ከተማ ደጋፊዎችን አስወጡ እያለ ህዝቡ እየጮኸ ነው ሲሉ የሚደርሱን መረጃዎች ያሳያሉ።

የትግራይ የበላይነት ይብቃ፣ ወያኔ ይውደም፣ በወያኔ አንገዛም፣ አማራ ነን እኛ፣ ለከፋፋዮች የማንተኛ በማለት በተለያዩ የሃገሪቷ አካባቢዎች አገዛዙን በመቃወም እየተነሱ የሚገኙት የተቃውሞ ድምጾች በወልዲያም እየተስተጋባ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።

ህዝባዊ ተቃውሞው ተጋግሎ በመቀጠሉ የመንግስት ወታደሮች እና የክልሉ ፖሊሶች በአስለቃሽ ጭስ ህዝቡን ለመበተን ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል። ተሽከርካሪዎችና ሆቴሎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰ እንደሆነና የመንግስት ወታደሮች ተኩስ መክፈታቸውም ተሰምቷል።