ደቡብ ሱዳን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (drones) ጥቅም ላይ እንደምታውል አስታወቀች

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

የደቡብ ሱዳን መንግስት ብዙ ሚሊዮን ዶላር በማፍሰስ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (drones) ጥቅም ላይ እንዳዋለ ተዘገበ። 

እነዚህ ውድ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በዋናዋ ከተማ በጁባ ያስቸገረውን የወንጀል ተግባርን ለመቆጣጠር ስራ ላይ እንደሚውሉ ተዘግቧል። ወንጀልን ለመከላከል ከሰው አልባ አውሮፕላኖች በተጨማሪ የደህንነት ካሜራዎችም ስራ ላይ እንደሚውሉ ተገልጿል። እነዚህ ሰው አልባ አውሮፕላኖችና የደህንነት ካሜራዎች ለጊዜው በእስራኤል ኩባንያ ስር ሆነው ስራቸውን እንደሚጀምሩ ታውቋል።

በዋናዋ ከተማ ጁባ አየር የሚበሩት ሁለት ሰው አልባ አውሮፕላኖች በ11 ካሜራዎች በመታገዝ ወንጀል የመዋጋቱን ስራ እንደሚጀምሩ የእስራኤሉ ኩባንያ የፕሮጀክት አስተባባሪ ተናግረዋል።

የጁባን ከተማና ነዋሪዎች ደህንነት ለመጠበቅ ቃል በገቡት መሰረት ሰው አልባ አውሮፕላኖችና ዘመናዊ ካሜራዎች በከተሟዋ ጥቅም ላይ እንዲውል መወሰናቸውን የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ተናግረዋል።

የተመረጡ ደቡብ ሱዳናዊያን  እነዚህን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እንዴት መምራትና መቆጣጠር የሚያስችላቸውን ስልጠና ከወሰዱ በኋላ የእስራኤሉን ኩባንያ ተክተው እንደሚሰሩ ተዘግቧል።

ከስድስት አመት በፊት ከሱዳን ነጻነቷን ብታውጅም፣ ደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነትና ግጭት በተደጋጋሚ እያስተናገደች እንደሆነ ይታወቃል።

ደቡብ ሱዳን ካጋጠማት ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ  በተጨማሪ ባለስልጣናቷም በከፍተኛ የሙስናና የምዝበራ ቅሌት እንደተወዘፉ ይነገራል።