የጠ/ሚ ሀ/ማርያም የግብጽ ጉብኝት እንዲሰረዝ ተጠየቀ

አባይ ሚዲያ ዜና
አክሊሉ ታደሰ

ከ18 በላይ የሆኑ የግብጽ ፓርላማ አባላት የጠ/ሚኒስትር ሀይለማርያም በግብጽ ፓርላማ ተገኝተው ንግግር ለማድረግ የተያዘው ቀጠሮ እንዲሰረዝ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለፓርላማው አፈ- ጉባኤ ማቅረባቸው ታወቀ፡፡

የግብጽ ፓርላማ አባል የሆኑት አብዱል ሀሚድ ከማል ከ18 ተጨማሪ የፓርላማ አባላት የፈረሙበት ይህ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር በፓርላማቸው ተገኝተው ንግግር ለማድረግ የተያዘው ቀጠሮ እንዲሰረዝ ጠይቀዋል። አስቸኳይ ያሉትን ለፓርላማው አፈ-ጉባኤ አሊ አብደላ ያቀረቡት ደብዳቤ፣ ፓርላማው የአባይ ግድብ በግብጽ ላይ ስለሚያመጣው አደጋ እንዲወያይ መጠየቃቸውን ግብጽ ኢንዲፔንደንት የተሰኘ ድረገጽ አስነብቧል፡፡

የፓርላማው አባላት ጠ/ሚንስትሩ የግብጽ የፓርላማ ተወካዮችን ለመጎብኘት የተያዘው ቀጠሮ እንዲሰረዝ በጠየቁበት ደብዳቤም ላይ የጠ/ሚንስትሩ ጉብኝት በግብጽ ላይ ግፊት ለማድረግና አለምን በግብጽ ተቃራኒ  ለማቆምና የግድቡን ግንባታ ለማስቀጠል ድጋፍ ለማግኘት ነው በሚል እንደሚያሳስባቸው በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡

የግብጽ ውሃ ቀይ መስመር የተደረገበትና የግብጽ ብሄራዊ ደህንነትን በተመለከተ ዋነኛ ጉዳይ በመሆኑ በሌሎች እውቅና ከማግኘቱ በፊት የጠ/ሚንስትሩን በፓርላማ መገኘት እንዲሰረዝ መጠየቃቸውን ይፋ እናደርጋለን ብለዋል። የፓርላማ አባላቱ ለፓርላማው አፈ-ጉባኤ ባቀረቡት ደብዳቤ ቅሬታቸውን ከመግለጻቸው በተጨምሪ፣ ከኢትዮጵያው ጠ/ሚንስትር ይልቅ ከሃገሪቱ የእርሻና መስኖ ባለስልጣን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ግብጻውያን ኤክስፐርቶች የአባይ ውሃን በተመለከተ እየተካሄደ ስላለው ውይይትና የደረሰበትን ሁኔታ ለመወያየት ጥሪ ማድረጋቸው ለንባብ እንዲበቃ ተደርጓል፡፡