በመቀሌ ፍትህን በመጠየቅ ተቃውሞ ተደረገ በንብረት ላይም ጥቃት ተፈጸመ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

ወደ ወልዲያ የመጡ የመቀሌ እግር ኳስ ደጋፊዎች ባሳዩት ስርአት የለሽነት ምክንያት በወልዲያ የተፈጠረው ግጭት ወደ መቀሌም ማምራቱ ተሰምቷል።

በደጋፊዎች ቅጥ ማጣት ተቆጥቶ ወደ አደባባይ በወጣው የወልዲያ ህዝብ ላይ የመንግስት ወታደሮች እርምጃ መውሰዳቸው ይታወሳል።

የህዝብ ቁጣው ወደ እምቢተኛነት በመቀየሩ የመንግስት ወታደሮች በወሰዱት እርምጃ ንጹሃን ነዋሪዎች መገደላቸውም ታውቋል። 

በወልዲያና በአከባቢውም ውጥረቱ ተስፋፍቶ የተወሰኑ ንብረቶች በተወረወሩ ድንጋዮች ሲሰባበሩ የተቃጠሉም እንዳሉ ተዘግቧል።

የወልዲያ የህዝብ ቁጣና አመጽ በመቀሌ ከተማም ቅርጹን ለውጦ የመቀሌ እግር ኳስን ድርጊት ወደማውገዝ እንደተቀየረ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። በመቀሌ ከተማ ለተቃውሞ ወደ አደባባይ የወጡት ሰዎች በወልዲያ የደረሰውን ጥቃት በመኮነንና በማውገዝ እንደሆነም ታውቋል። ተቋውሟቸውን ለማሰማት ወደ አደባባይ የወጡት የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ፍትህን እንፈልጋለን ፍትህ ለመቀሌ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች እያሉ ሲጮሁ እንደነበረም ተሰምቷል።

በወልዲያ ከተማ በንብረቶች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ብድር ለመመለስ በሚመስል መልኩ በመቀሌም ንብረቶች እየተመረጡ ጥቃት እንደደረሰባቸው የአይን እማኞች ተናግረዋል። ብዛት ያላቸው የክልሉና የፌዴራል ፖሊስ በመቀሌ ከተማ ከፍተኛ ቁጥጥር ለማድረግ እንደተመደቡም ተሰምቷል።