እየሩሳሌም ቀይ መስመር ናት በማለት የቱርክ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን አስጠነቀቁ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ ለማድረግ አለም አቀፍ እውቅና እንዲሰጣት የሚደረገውን ጥረት የቱርክ ፕሬዝዳንት በጽኑ እንደሚቃወሙት አሳወቁ።

እየሩሳሌም ለሙስሊሞች የቀይ መስመር እንደሆነች ፕሬዝዳንት ኤርድዋን ለዩናይትድ ስቴትስ አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ በቴሌቭዥን በተሰራጨው ንግግራቸው መልክታቸውን አስተላልፈዋል። እስራኤል እየሩሳሌምን ዋና ከተማ ካደረገች ከቱርክ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን እንደሚያቋርጡ የቱርኩ ፕሬዝዳንት አስጠንቅቀዋል።

እስራኤልም በበኩሏ የቱርክ ፕሬዝዳንት ምን ግዜም እስራኤልን ባገኙት አጋጣሚ ከመኮነን እንደማይቆጠቡ በማስታወስ ዛቻቸውንም ከቁብ እንደማትቆጥረው አስታውቃለች።

ዩናይትድ ስቴትስ ቴላቪቭ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም ለማዘዋወር እንቅስቃሴ መጀመሯን ተከትሎ የተለያዩ አገራት ወቀሳ እያቀረቡ ናቸው። የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚንስትርን ጨምሮ የአረብ አገራት እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት መዘዝ እንደሚያመጣ በመናገር ሂደቱን ኮንነዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ቴላቪቭ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም ካዘዋወረችና የእስራኤል ዋና ከተማ እንደሆነች እውቅና ከሰጠች በአለም የመጀመሪያዋ አገር እንደምትሆን ሪፖርቶች ያሳያሉ።

እስራኤል ምን ጊዜም እየሩሳሌም ዋና ከተማዋ መሆን እንዳለባት ብትገልጽም ፍልስጤሞች በተቃራኒው ምስራቁ እየሩሳሌም የወደፊቷ የፍልስጤም ግዛት ዋና ከተማ እንደምትሆን ይናገራሉ።