ባለፈው ሳምንት ወልዲያ ተቀስቅሶ በነበረው ተቃውሞ ምክንያት ሱቆቻቸውን የዘጉ ነጋዴዎች አልከፈቱም፣ የህወሓት አባላትም ለአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርተዋል

የተለየ እንክብካቤ እየተደረገላቸው በወልዲያ ከተማ ቁልፍ ሆቴሎችንና ሱቆችን በመቆጣጠር በሕዝቡ ላይ የስለላ ተግባር ይፈጽሙ የነበሩ የህወሃት ደጋፊ ነጋዴዎች ሆቴሎቻቸውን እና ሱቆቻቸውን እስከ አሁን ድረስ እንዳልከፈቱም፤ በዚህም ምክንያት የተቸገረው የከተማው አስተዳደር  አባላትን ለአስቸኳይ ስብሰባ እንደጠራ ለትንሳኤ ሬዲዮ የደረሰው ዜና ገለፀ።

በከተማው ውስጥ ተቆጣጥረውት የነበረውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማካሄድ ስጋት ስለአደረባቸው ሱቆቻቸው እስከ አሁን ድረስ ዝግ ናቸው። በተጨማሪ ሀሙስ ቀን በሚውለው ሀራና ጎብየ ተብሎ በሚታወቀው የገበያ ቦታ ላይም የመንግሥት ደጋፊ የሆኑ ነጋዴዎች አለመገኘታቸው ታውቋል።

እነዚህ የከተማዋን ዋና ዋና ሆቴሎችና ሱቆች በባለቤትነት የያዙት ነጋዴዎች ሀራና ጎብየ በመባል በሚታወቀው የገበያ ቦታ ላይም ለመገበያየት ምቹ የሆኑ (ዐይን ቦታዎችን)ከማገኘት ጀምሮ የተለያዩ ድጎማዎችን እስከማገኘት ድረስ ከባለሥልጣናት እገዛ እየተደረገላቸው የገበያውን ቦታ በቀዳሚነት እንደተቆጣጠሩት ይታወቃል።

እንደዚሁም በወልዲያ መናኸሪያም ከመንግሥት ጋር አብረዉ በመስራት ሹፌሮችን በመሳደብ፣ በመሰለል፣ በማሳሰር እና ከስራ በማሳገድ ይታወቁ የነበሩ የተሽከርካሪ ባለቤቶችና ሹፌሮች ባካባቢው አልታዩም። ከመንግስት ጋር በአላቸው ትስስር በመመካት በሌላው ወገን ላይ ያደረጉት መጥፎ ስራ የቱን ያህል ሌላውን ወገን እንዳስቆጣ ስለአወቁ ወደቦታው አለመምጣታቸው አያስደንቅም በማለት መረጃውን ያቀበሉት የአካባቢው ኗሪዎች ገልፀዋል።

ሁኔታው ያሳሰበው የከተማው አስተዳደር የመንግስት ካድሬዎችን ለአስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል። የተለመደውን የዉሸት ቃል በመግባት ሕዝቡን አግባብተው ሁኔታውን በማብረድ የነጋዴውን ስጋት የሚቀንሱ ሥራዎችን እንዲሰሩና መታሰር የሚገባቸውን ተቃዋሚዎች የመለየት ስራ እንዲሰሩ ለካድሬዎች መመሪያ ለመስጠት ታስቦ እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የወልዲያ፣ የራያና ቆቦ አካባቢ ኗሪዎች የጀመሩትን ተቃውሞ አጠንክረው ለመቀጠል መወሰናቸውን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉት የመረጃ ምንጮቹ  ገልፀዋል።