የሶማሌ ልዩ ሃይሎች የቀበሌን ሊቀመንበር ጨምሮ ስድስት ሰላማዊ ሰዎችን ገደሉ፣ ከልዩ ሃይልም የተገደለ አለ ተባለ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

በሶማሌ ልዩ ሃይል እርምጃ የሰላማዊ ነዋሪዎች ህይወት በየቀኑ እየተቀጠፈ እንደሆነ ቪኦኤ ከነዋሪዎች ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ ዘግቧል።

እንደ ዘገባው ከሆነ አቶ መሃመድ አዴ የሚባሉ የላከሌ አረዳ ቀበሌ በሶማሌ ልዩ ሃይል በተወሰደባቸው እርምጃ በጥይት ተመተው ተገድለዋል።

የሊቀመንበሩ ቤተሰቦችና ወዳጆች ለጠፋው ነፍስ ቂም በቀል ካልተከፈለ በስተቀር ሃዘን እንደማይቀሙጡ መናገራቸውን አንድ እማኝ ለሬዲዮው ገልጿል። ሊቀመንበሩን ለመግደል ከተሰማሩት ልዩ ሃይሎች መካከል አንዱ  ሊቀመንበሩ እራሳቸውን ለማዳን  በተኮሱት ጥይት መገደሉም ተሰምቷል። የሶማሌ ልዩ ሃይሎች በሊቀመንበር መሃመድ አዴ ላይ የግድያ እርምጃ ከወሰዱ በኋላ  ስድስት ንጹሃን ነዋሪዎችን መግደላቸውም ተነግሯል።

ልጃ ገረዶችም በሶማሌ ታጣቂዎች ታፍነው ወደ ማይታወቅ ቦታ እንደተወሰዱም ሲዘገብ ጤና ጣቢያዎችና ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የመንግስት መስሪያ ቤቶችም ተዘግተዋል።

በአገር ሽማግሌ የተፈጸመውን እርቅና ሰላም እንዴት ትቀበላላችሁ በማለት ዳግም በጎሳዎች መካከል ግጭት እዲፈጠር ሆን ተብሎ እየተሰራ እንደሆነም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።