የአዲስ አበባ ኗሪዎች ከሱማሌ ክልል ለተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች የሚውል የእርዳታ ማሰባሰቢያ ኩፖኖችን እንዲገዙ እየተገደዱ መሆኑ ተነገረ

በአዲስ አበባ ከዓርብ ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ ትእዛዝ በተላለፈበት የኩፖን ሽያጭ ላይ ከየክፍለ ከተማዉ የተመረጡ ግለሰቦች ተመድበው ቤት ለቤት እና በንግድ ቦታዎች በመዘዋወር ባለ አንድ ሺህ፣ ባለ አምስት መቶ፣ ባለመቶ እና ባለሀምሳ ብር ኩፖኖችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

ለትንሳኤ ሬዲዮ የደረሰው መረጃ እንደሚያሳየው በአዲስ አበባ  የሽያጭ ሁኔታው ከታየ በኋላ ሽያጩ በክልል በተሞችም እንደሚጀመር መታዘዙን ያመለክታል። ከዚህ በፊት  በግፍና በገፍ ከሱማሌ ክልል ለተፈናቀሉት የኦሮሞ ወገኖች ሕዝቡ በእራሱ ተነሳሽነት ተፈናቃይ ወገኖቹን ለመርዳት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ኮንሰርት በማካሄድ ላይ እያለ የገንዘብ ማሰባሰቡ ሂደት እንዲቋረጥ ያደረገና ለመፈናቀላቸው ምክንያት እራሱ መንግሥት ሆኖ ሳለ ለእርዳታ ገንዘብ አሰባስባለሁ ማለቱ ብዙዎችን ማበሳጨቱን የዜናው ምንጮች ገልጸዋል።

ሻጮቹ ለእርዳታ የተባለውን ኩፖን ከሚሸጡት ግለሰቦች ያልገዙ ሰዎችን ከመንግሥት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ ያልሆኑ በመባል ተመድበው መንግስትም እነሱ ትብብር ሲጠይቁ ምላሽ እንደማይሰጣቸው ንገሩ ተብለናል በሚል ማስፈራሪያ የማስገደጃ ቃል ሲናገሩ መደመጣቸው ተሰምቷል።

በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ከአንድ መቶ እስከ አንድ ሺህ ብር፣ የግል መስሪያ  ቤት እና የመንግስት ሰራተኞችን ደግሞ አንድ መቶ እና ሀምሳ ብር እንዲአስከፍሉ መመሪያ እንደተሰጣቸው ከውስጥ ምንጮች ለማወቅ ተችሏል።

የህወሀት አገዛዝ በየጊዜው እያጋጠመው  ያለውን የገንዘብ እጥረት በተለያየ መልኩ አደጋ በሚያጋጥማቸው ወገኖች ስም እርዳታን እየሰበሰበ ወደ ካዝናው እንደሚያስገባ ይታወቃል። በቆሼ የቆሻሻ ክምር መናድ ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን እና መኖሪያቸውን ባጡ ወገኖች ስም የተሰበሰበው ገንዘብ ደብዛ መጥፋት የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች በማስታወስ አሁንም  በተፈናቃይ ቤተሰቦች ስም ለመሰብሰብ  ባቀደው ገንዘብ ከዚህ የተለየ ምንም ነገር እንደማይደረግበት በእርግጠኝነት እየተናገሩ ነው።