የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኃላፊው ለልጃቸው ትምህርት ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ መክፈላቸው ታወቀ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ናትናኤል ኃይለማርያም

በብሔራዊ  መረጃና ደህንነት መሥሪያ ቤት ውስጥ በዋና ዳይሬክተርነት የሚሠሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ ልጆቻቸውን በአሜሪካን አገር ኢንዲያና ስቴት በሚገኘው ማንቼስተር ዩኒቨርስቲ በሚሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ወጭ እያደረጉ እንደሚያስተምሩ ታውቋል። አቶ ጌታቸው ለልጃቸው ለልዕልቲ ጌታቸው በአንድ አመት የምግብ እና የመጠለያ ወጭዋን ሳይጨምር ለትምህርት ብቻ 1.6 ሚሊዮን ብር እንደከፈሉ ታውቋል።

አብዛኛው የመንግስት ባለስልጣናት የአገሪቷን ሃብት ያለ አግባብ እንደሚያባክኑ የሚታወቅ ሲሆን ልጆቻቸውን በውጭ አገር ለትምህርት እንደሚልኩም ይታወቃል። የኢትዮጵያ የትምህርት አሰጣጥ በአለም ላይ ካሉት አገራት የመጨረሻውን ደረጃ በያዘበት በአሁኑ ወቅት የመንግስት ባለስልጣናት ልጆቻቸውን በአለም ላይ በሚገኙት ምርጥ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች እየላኩ ከድሐው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተመዘበረ ገንዘብ እንደሚያስተምሩ ይታወቃል።

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እና የከፍተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በአቶ ጌታቸው አሰፋ የደህንነት ሰዎች ስቃይ በመቀበል ላይ ሲሆኑ፣ ገሚሱ እስር ቤት ገሚሱም እየተገደለ ባለበት ወቅት የደህንነቱ ሐላፊ ግን ልጆቻቸውን በውጭ ሀገር በኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘብ ማስተማራቸው ብዙዎችን አስቆጭቷል ።

የደህንነት መስሪያ ቤቱ የአገዛዙን ስልጣን ለማቆየት ከወታደሩ ጋር በመቀናጀት በአገሪቷ ውስጥ ከፍተኛ ሰቆቃ እና ግድያ እንደሚፈጽም በርካታ መረጃዎች ያሳያሉ። የብሔራዊ መረጃና ደህንነቱ የአገሪቷን ሰላም እና የአገሪቷን ሃብት መጠበቅ ሲገባው ሰላሟን በማፍረስም ሆነ ሃብቷን በመዝረፍ በዋናነት መገኘቱ ሐገሪቷ ያለችበትን ከፍተኛ ችግር ያሳያል ሲሉ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ።