የኢትዮጵያ ሕዝብ አገዛዙ ሳይወርድ ትግሉን አያቆምም ተባለ

አባይ ሚዲያ ዜና
ናትናኤል ኃይለማርያም

በኢትዮጵያ አገዛዙን በመቃወም ጋብ ያለ መስሎ የነበረው ሕዝባዊ ቁጣ አሁንም በተጠናከረ ሁኔታ በተለያዩ ቦታዎች በከፍተኛ የሕዝብ ቁጣ እንደገና መቀስቀሱ አገዛዙን ዳግም ወደማይወጣበት ጭንቀት ውስጥ እንደከተተው ለማወቅ ተችሏል።

በወልቂጤ ዩኒቨርስቲና በአዋሳ ዩኒቨርስቲ በተማሪዎች የተነሳው ይኸው አገዛዙን የሚቃወመው ሰልፍ በከፍተኛ ደረጃ የአካባቢውን ሕዝብ አካቶ እንዳመሸ ታውቋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የስርዓቱን ግድያና አፈና ተቃውመው ከአምቦ እስከ ነቀምት ባሉት ቦታዎች የሥራ ማቆም አድማ መጠራቱን መዘገባችን ይታወቃል።

በአዲስ አበባ የአለው የሕዝብ ስሜት አገዛዙን ጭንቀት ውስጥ ስለአስገባው አዲስ አበቤዎችን በተለያየ የስብሰባ ወጥመድ ለማዘናጋት በማሰብ በድምፅ ማጉያ ጥሪ ያስተላልፍ እንደነበር ሲታወቅ በፓርላማው ውሎም የኦህዴድ አባላት ስብሰባው እንዲቋረጥ ማድረጋቸው ታውቋል።

የአዲስ አበባው ፓርላማ አገዛዙ በአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ጉዳይ ለመወያየት ፍላጎት ቢያሳይም በቅድሚያ ስለተፈናቀሉትና ስለተገደሉት ኦሮሞዎች ተነጋግረን መፍትሄ ማግኘት አለብን፣ ይኽን ትልቅ ጉዳይ ወደ ጎን በመተው ስለአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም የምንነጋገርበት ጉዳይ የለም ሲሉ የኦህዴድ ፓርላማ አባላቶች አስታውቀው ስብሰባው እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ዜና፣ የፓርላማ አባሏ ወ/ሮ ነኢማ አሕመድ  “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካላነጋገሩን ወደ ሥራ አንገባም ብለናል” ብለው መናገራቸውን በአሜሪካ የአማርኛው ድምጽ ክፍል በሰጡት ቃለ መጠይቅም መግለፃቸው ይታወሳል።

በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የሰፈረው የመከላከያ ሰራዊትም ከህዝቡ ተቃውሞ ሲገጥመው እና ትብብርም የተነፈገው እንደሆነ እና ወደ ሱቆች ሄዶ ውሃ እንኳን መግዛት ያልቻለበት ሁኔታ መፈጠሩንም ለማወቅ ተችሏል።

የመከላከያ በክልሎች መስፈርን አስመልክቶ ሕዝቡ ተቃውሞውን በተለያዩ ቦታዎች እያሰማ መሆኑ ሲታወቅ በኦሮምያ አካባቢ መንገዶችን በመዝጋት ተቃውሟቸውን እያሳዩ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።