አታህሣስ ፲፱ ቀን ፪ ሺህ ፲ ዓ. ም

December 28, 2017

ከአንድ ወር በላይ በመቀሌ ከተማ ስብሰባ ላይ የሰነበተው የህወሓት አመራር ካወጣው መግለጫ እንደተረዳነው፣ “በሥልጣን የባለጉትን አስወግደንና ጥልቅ ተሃድሶ አድርገን በአዲስ መንፈስ ስብሰባችን አጠቃለናል” ይላል። 

የተባለው እድሳት ሃቀኛ ይሁን አይሁን ለማወቅ የፖለቲካ ምርምር የሚያሻው አይመስለንም። ከአመራር በጡረታ የተገለሉ ሁሉ የታደሙበት ስብሰባ፣ ዓላማው በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሤራ ለመሸረብ የተደረገ ቅድመ-ዝግጅት ነበር። አንዱን የሥልጣንና የሀብት ተቀናቃኝ ቡድንን አግልሎ ሌላውን ለማጠናከርና ሕዝብን ለማደናገር የተዶለተ ስብሰባ መሆኑን የውጤቱም ሆነ የተሰብሳቢዎች ዓይነት በግልጽ ያሳያል። 

ይህ ስብሰባ “በሙስና ተበክለናል”፣ “አንዱ ለሌላው አልታዘዝ ብሏል” በሚል ድርጅታቸውን የበለጠ አጠናክረውና የኤኮኖሚና የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ከሥልጣን ለማስወገድ ሲካሄድ የከረመ ሽኩቻ እንጂ የሀገራችንን ችግር ለመፍታትና ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ለማሳየት የተደረገ ሰብሰባ አልነበረም።  ዕውነት የተሃድሶ ስብሰባ ቢሆን ኖሮ፣ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የዴሞክራሲ እጦት የመነጋገሪያ አጀንዳ አድርጎ የመፍትሄ ሀሳብ ማመንጨት አስፈላጊ በሆነ ነበር።  ጣራ የነካውን  የኤኮኖሚ ችግርም አስመልክቶ በሰፊው ተወያይቶ መፍትሄ ቢሻ ኖሮ እውነትም አገዛዙ አስፈላጊና ዕውነተኛ ተሃድሶ ተመኝቶ ነው በተባለ ነበር። 

ከኤኮኖሚው ቀውስ በተጨማሪም ህወሓት ባመጣው የጎሣ ፖለቲካ ምክንያት የተከሰተውን የሕዝብ ግጭት በሰፊው ተነጋግሮ መፍትሄ መስጠት ከአንድ ገዥ ፓርቲ የሚጠበቅም ነበር። ይሁን እንጂ አገዛዙ ራሱ እየተነኮሰ የተከሰተ ግጭት ስለሆነ ስብሰባውን ተከትሎ የወጣው መግለጫ ላይ አንድም የሕዝብን ብሶት ያካተተ ጉዳይ አለመኖሩን ለሚረዳ ሰው የጎሣ ግጭቱን የሥልጣን ማራዘሚያ መፍትሄ አድርጎ የያዘው መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም።

አሁን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እየተቀጣጠለ ስላለው ፀረ-አገዛዙ እንቅስቃሴ አንድም ነጥብ አንስቶ ለመወያት አለመሞከሩ የሚያመላከተውም እራሱን የበለጠ አጠናክሮ የሕዝቡን ጥያቄ በኃይል ለማዳፈን ያለውን ዕቅድ ከግምት ውስጥ ማስገባትን ነው። ለነገሩ እንዲያው እናንሳው ብለን እንጂ ሀወሓት ሕዝባዊ ጥያቄዎችን አንስቶ መፍትሄ ማፈላለግ ባህሪው የማይፈቅድለትና ምላሽም የማይጠበቅ መሆኑን ጠንቅቀን እንረዳለን።  አባይ ወልዱን አወርዶ በደብረጽዮን መተካት ተሃድሶ አይደለም። አዜብ ከሥራ አስፈጻሚነት ወረደች አልወረደች ህወሓትን ዴሞክራሲያዊ አያደርገውም። ተጠቃሾቹ ምንጊዜም ከአንድ ወንዝ የተቀዱ፣ በፀረ-ዴሞክራሲያዊ ዋንጫ በጋራ ሲጠጡ የኖሩ ፀረ-ሕዝቦች ናቸውና! የሕዝብ ወገን ሆነው አያውቁም፣ ሊሆኑም ከቶውኑም አይቻላቸውም። 

በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እንደሚናኘው፣ ደብረጽዮን ከአባይ ወልዱ ይሻላል የሚለው አባባል እንደፈረስ ለሚጋልቧቸው ተከታዮቻቸው ለአንድ ሰሞን የመነጋገሪያ አጀንዳ የሚውል የፕሮፖጋንዳ ፍጆታ እንጂ ዕውነተኛውን ሁኔታ አያመላክትም። የህወሓት አመራር ከስብሰባ በወጣ በሳምንቱ፣ በአዲግራትና በመቀሌ ዩኒቨርስቲዎች በአማርኛና ኦሮሞኛ ተናጋሪ ተማሪዎች ላይ የግድያና የድብደባ ወንጀል ሲፈጸም አንድም እርምጃ አለመውሰዱ፣ “መታደስ” ሳይሆን ያው የተጠናወተው የዘረኝነት አባዜ ያለቀቀው መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው።  በዚህ ረገድ የጎሰኛው ሥርዓት ሆን ብሎ እየፈጸመው ያለውን ወንጀል የትግራይ ምሁራንና የአገር ሽማግሌዎች ድርጊቱን በማውገዝ ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጡ ይጠበቃል። በሌላ በኩል አገዛዙ በጎንደር፣ በወልድያ፣ በደብረማርቆስና በአምቦ ዩኒቨርሲቲዎች በሰላማዊ መንገድ የዴሞክራሲ ጥያቄ ባነሱ ተማሪዎች ላይ የጭካኔ ብትሩን ሲያሳርፍ ማየት የዘረኝነት ቋቱ ሞልቶ እየፈሰሰ መሆኑን በግልጽ አመላካች ነው። 

የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎች ሆይ!

የኢትዮጵያ ተማሪዎች ለዴሞክራሲና ለእኩልነት በተደረገው ትግል ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሰፊው ሕዝብ መብቶች እንዲከበሩና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሠረት ታግለዋል፣ ከፍተኛውን የሕይወት ዋጋም ከፍለዋል።  በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች የምትገኙ ተማሪዎች ሀገሪቷን ተረካቢዎች በመሆናችሁ፣ ራሱን ለሕዝብ አሳልፎ ከሰጠው ከዚያ ትውልድ በመማር የሕዝብ ጥያቄዎችን አጉልቶ በማንሳት በኅብረት እንድትታገሉ ይጠበቅባችኋል። የህወሓትን የዘር ፖለቲካ ሰብራችሁ በመውጣት በሀገራችን ሰላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን በሚደረገው ትግል እንደቀድሞ ተማሪዎች በኅብረት ቆማችሁ መታገል ይገባችኋል። ዘረኝነት መርዝ ነው። እናንተ አገር ተረካቢዎች ዘርኝነትን በመቃወም ለሕዝብና ለሀገር አንድነት ልትታገሉ ይገባል እንላለን።  በአንዳንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች ያላችሁ ተማሪዎች የምታሳዩትን ከዘር የፀዳ እንቅስቃሴ ኢሕአፓ (አንድነት) እጅግ ያደንቃል፣ ከልብም ይደግፋል። ኢሕአፓ (አንድነት) በዚህ አቋማችሁም ተጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ እያሳሰበ የሚቻለውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል።  

የተቃዋሚ ኃይሎች ሆይ!

እንዳለፉት ዓመታት የህወሓት ሕዝብን በኃይል ረግጦ ለመግዛት መሞከር የሕዝብን አልገዛም ባይነት አጠናክሮ ትግሉን እንዲያፋፍም ያደርገዋል እንጂ የአፈና ሥርዓቱን በሕዝብ ላይ ጭኖ ለመቀጠል የማያስችለው መሆኑን ሊረዳው ይገባል። ሕዝባችን መብቱን እንዲጎናጸፍ የችግሩ ምንጭ የሆነውን አምባገነንና አፋኝ አገዛዝ በጋራ መታገል የግድ ነው።  ስለሆነም ተቃዋሚዎች ይህን መሠረቱ የተናጋውን ህወሓት-መራሹን አገዛዝ በአንድ ላይ ተባብረን አገራችንንና ሕዝባችንን ማዳን ወቅቱ የሚጠይቀው ነው።  በሀገራችን ላይ የተደቀነውን አደጋ ማስወገድ የግድ ነውና ብሄራዊ አንድነትን ያማከለ የትግል ግንባር መፍጠር ይዋል ይደር የሚባል አይደለምና በተባበረ ክንድና በተቀናጀ ትግል ኢትዮጵያን እንታደጋት!  በዚህ ረገድ ኢሕአፓ (አንድነት) ከአሁን በፊትም ደጋግሞ እንደገለጸው አሁንም የድርሻውን ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ ያረጋግጣል።

ክብርና ልዕልና ለኢትዮጵያ!