አቶ አባዱላና አቶ በረከት ወደ ስራቸው ተመለሱ ተባለ

አባይ ሚዲያ ዜና
አክሊሉ ታደሰ

እስከ መጨረሻው በውዝግብ የቆየው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ድንገት ስብሰባውን ማጠናቀቁ ተሰማ። አቶ አባዱላ ገመዳና አቶ በረከት ሲሞን ከነበሯቸው የመንግስት ስራ ሀላፊነቶች ያቀረቡትን የስራ መልቀቂያ ጥያቄ አንስተው ወደ ሰራ ለመመለስ መስማማታቸውም ተነግሯል።

ለአስራዘጠኝ ቀናት ያለአንዳች ስምምነት የቆየው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ያለውጤት መቋረጡም ተነግሯል። ይህ በሆነ ማግስት በድንገት የስራ አስፈጻሚው ስብሰባም መጠናቀቁ ተሰምቷል። የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ በስብሰባው የደረሰባቸውን ውሳኔዎች ነገ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ መጠናቀቅ ድንገተኛ ዜናን ተከትሎም አቶ አባዱላ ገመዳና አቶ በረከት ሲሞን ከነበሯቸው የመንግስት  ስልጣን በስርአቱ ላይ አለን ባሉት ቅሬታ ምክንያት በፈቃዳቸው ስራና ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ያቀረቡትን ጥያቄ ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት ገሸሽ በማድረግ ወደ ሰራ ለመመለስ መስማማታቸውም ተሰምቷል።

በተለይ የአቶ አባዱላ ገመዳን የስራ መልቀቂያ በተመለከተ ስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ተቀብዬዋለሁ ካለ ሶስት ቀናት በኋላ በተቃራኒው ወደ ስራ ለመመለስ መስማማታቸው መገለጹ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።